Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችየተማሩ ሙስሊም ዜጎቿ ‘የሚሸሿት’ ፈረንሳይ

የተማሩ ሙስሊም ዜጎቿ ‘የሚሸሿት’ ፈረንሳይ

አውሮፓዊቷ ፈረንሳይ በቅርብ ዓመታት ሙስሊሞችን ከመግፋት ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ሥሟ አደባባይ ይውላል፡፡ ሙስሊሞችን በመግፋት የምትወቀሰው ፈረንሳይ፣ ከሙስሊሙ ዓለም በርካታ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች ተቀብላ ዜግነት የሰጠችው እ.አ.አ በ1970ዎቹ አጋማሽ ነበር፡፡ ወደ ሀገሪቱ የገቡ ሙስሊም ስደተኞች በመቶ ሺዎች ይቆጠራሉ፡፡

በወቅቱ ስደተኞች ወደ ትልልቅ ከተሞች በመሄድ ድጎማ እየተሰጣቸው ኑሮን ሊገፉ ቢሞክሩም ሀገሪቱ በኢኮኖሚ ተንኮታኩታ ስለነበር በስቃይ ውስጥ ከማለፍ አልዳኑም፡፡ ወደ ፈረንሳይ የገቡት ስደተኞቹ ቢከፋም ቢለማም ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሀገሬውን መስለው እየኖሩ ነው፡፡

ፈረንሳይ ከዚህ ክስተት ሀምሳ ዐመታት በኋላ እነዚህን ጨምሮ ከነዋሪዎቿ ውስጥ 9 በመቶ ሙስሊም ነዋሪዎችን ይዛለች፡፡ ሆኖም በ2019 በወጣ ሪፖርት ከጠቅላላ ሙስሊም ማኅበረሰቡ ውስጥ 42 በመቶ የሚሆኑት ‘በሃማኖታችን ምክንያት መገለል ይደርስብናል’ የሚል እምነት አላቸው፡፡ በዚህ መገለል ሳቢያ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ማነሱን እንዲሁም በበቂ መጠን ውክልና ማግኘት አልቻልንም የሚሉ ናቸው፡፡

እነዚህ ድምጾች ባለፉት ዓመታት ተባብሰው ሙስሊም ነዋሪዎች ፈረንሳይን ለቀው ሥራ ፍለጋ ወደ ሌላ ሀገር ለመሄድ እንደተገደዱ ነው፡፡ “ፍራንስ 24” ቴሌቪዥን አዲስ ባወጣው ዘገባ፣ ፈረንሳይ ለሙስሊም ዜጎቿ የማትመች ሀገር መሆኗን የሚናገሩ ድምጾችን ይዞ ወጥቷል፡፡

የቴሌቪዥን ጣቢያው ያናገራቸው የዘር ግንዳቸው በተለይ ከሰሜን አፍሪካ እና ምዕራብ አፍሪካ የሚመዘዙ ሙስሊም ዜጎች፣ ፈረንሳይ ውስጥ ከምንቀመጥ ‘በእኩልነት ወደምንታይበት ብንሄድ ይሻላል’ ብለው ወደ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች እና ሌሎችም ሀገራት ስደት የመረጡ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ትውልድ ሙስሊም ፈረንሳዊያን ሀገራቸው ውስጥ ሠርተው ለማደር ከሌላው ሁለት እጥፍ መልፋት ይጠበቅብናል የሚል አቤቱታም ያቀርባሉ፡፡ ወላጆቻቸው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደተወለዱበት ሀገር ቢመጡም፣ የእነርሱም ኑሮ አሰቃቂ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

ሥሙ ያልተጠቀሰ የ32 ዓመት ዕድሜ ያለው የዘር ግንዱ ከሰሜን አፍሪካ የሆነ ሙስሊም ፈረንሳዊ፣ በአሁኑ ጊዜ ዱባይ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ “እዚህ ሁላችንም እኩል ነን፤ አለቃህ ሕንዳዊ፣ ዐረብ አልያም ፈረንሳዊ ግለሰብ ሊሆን ይችላል፡፡ ሃይማኖቴም እዚህ ይበልጥ ተቀባይነት አለው” ብሏል፡፡ ተመሳሳይ አስተያየት የሰጠው የ33 ዓመት የቴክኖሎጂ ባለሞያም ባለቤቱ ነፍሰ ጡር ብትሆንም በቀጣይ የተሻለ ሰላማዊ ማኅበረሰብ ፍለጋ ወደ እስያ ሀገራት ለመሰደድ መዘጋጀታቸውን ተናግሯል፡፡

የሁለቱን ሙስሊም ፈረንሳዊያን ሐሳብ የሚያጠናክረው ፍራንስ24 ያናገረው ሦስተኛው ሰው ደግሞ በቢዝነስ ትምህርት የተመረቀ ነው፡፡ ባለ አምስት አሐዝ ደመወዝተኛው ፈረንሳዊ፣ “እዚህ ሀገር ውስጥ ታፍነናል” ሲል ምሬቱን ገልጧል፡፡ ይህ የቴክኖሎጂ ባለሞያ በሀገሪቱ ቴሌቪዥኖች “ለሁሉም ጥፋት የጦስ ዶሮ መደረጋችን ሰልችቶኛል” በማለት የሚደርስባቸውን ያስረዳል፡፡

ሙስሊም ፈረንሳዊያኑ ከዱባይ በተጨማሪ የእንግሊዟ ለንደን፣ የአሜሪካዋ ኒውዮርክ እና የካናዳዋ ሞንትሪያል መዳረሻቸው እየሆነ መጥቷል፡፡ በሙስሊም ዜጎቿ ስሞታ የሚቀርብባት ፈረንሳይ፣ አራምደዋለሁ በምትለው ሴኩላሪዝም ሰበብ የትኛውንም ዐይነት ሃይማኖታዊ ትዕምርት በአደባባይ እንዳይታይ ከልክላለች፡፡ ሀገሪቱ ከ2021 ጀምሮ በአደባባይ ኒቃብ እንዳይለበስ መከልከሏም በሥፋት ተቃውሞ የተሰማበት ነበር፡፡ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ሒጃብ እና አባያን በትምህርት ቤቶች ለመከልከል ሲወተውቱ መታየታቸውም አዲስ አይደለም፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular