ከቱኒዝያዊ አባት እና ከሞሮኳዊት እናት የተወለደው ሙሐመድ ቦላቢያር፤ እትብቱ የተቀበረው ፈረንሳይ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ነሐሴ ወር ላይ “የልጅነት ሕልሜ ነው” ላለው አንድ ክንውን ጉዞ ጀመረ፡፡ ጉዞው ወደ መዲና፤ ክዋኔው ደግሞ የዑምራ ሥነ ሥርዐት ነው፡፡
ሙሐመድ ከሚነሳባት ፈረንሳይ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያዋ መዲና ከተማ ለመድረስ 8 ሺሕ ኪሎ ሜትር ማቋረጥ ግድ ነው፡፡ ፈረንሳዊው ምዕመን ጉዞውን ለማድረግ ሲነሳ የአውሮፕላን በረራ ትኬት መቁረጥ አላስፈለገውም፡፡ ሌላ ዐይነት የትራንስፖርት አማራጭም አልተጠቀመም፡፡ ሙሐመድ ነሐሴ 12/2015 የጀመረውን ጉዞ ለማድረግ የመረጠው በእግሩ ነው፡፡
ፈረንሳዊው የዑምራ ተጓዥ ይህ ለምን ማድረግ እንደመረጠ ሲጠየቅ፤ “የልጅነት ሕልሜ ነው” ይላል፡፡ ሙሐመድ ማድረግ የፈለገው የውዱን ነቢይ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እና ባልደረቦቻቸውን ፈለግ መከተል ነው፡፡ ለዚህም እንደ ጥንቱ በጀመረው የእግር ጉዞ፣ ሳዑዲ ዐረቢያ ለመድረስ 13 ሀገራትን ማቆራረጥ ነበረበት፡፡
በርግጥ ሙሐመድ ለዚህ ፈታኝ ጉዞ ከመነሳቱ በፊት ለሁለት ዓመት ልምምድ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ጉልበቱን ሲያዳብር የቆየው ሙሐመድ፣ መዲና ለመድረስ ስዊዘርላንድ፣ ጣሊያን፣ ስሎቬንያ፣ ክሮሽያ፣ ቦስንያ፣ ሞንቴኔግሮ፣ አልባንያ፣ ሜቄዶንያ፣ ግሪክ፣ ቱርክ እና ጆርዳንን አቆራረጠ፡፡

ሙሐመድ ወደ መዲና ላደረገው ጉዞ ሲጠቀም የነበረው ካርታ ብቻ ነው፡፡ በጀርባው ባነገታት ትንሽዬ ቦርሳ እና በሚጎትተው ጋሪ ያስፈልጋሉ ያላቸውን ምግቦች፣ ለመኝታ እና ማረፊያ ሰዓት የሚጠቀምበትን ድንኳንም ሸክፎ ነበር፡፡ ሙሐመድ በጉዞው አንዳንድ ጊዜ ማደሪያውን ሲያደርግ የነበረው በመስጅዶች ነው፡፡ በመንገዱ ያገኙት ደጋግ ሰዎችም በቤታቸው እንዳሳረፉትም ያስታውሳል፡፡
ሙሐመድ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ነሐሴ ወር የጀመረውን ጉዞ በድል አጠናቆ ረቡዕ ግንቦት 7/2016 መዲና ከተማ ገባ፡፡ ወደ ከተማዋ ሲገባ ያገኙት የሳዑዲ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኞች ‘በመንገድህ ፈታኝ የነበረው ጉዳይ ምንድን ነው?’ ሲሉ ጠይቀውት ነበር፡፡ ሙሐመድ ለዚህ ጥያቄ በሰጠው ምላሽ ከባዱ ፈተና የአየር ጠባይ እንደነበር ተናግሯል፡፡ ሙሐመድ በስምንት ወራት የእግር ጉዞው፣ የአውሮፓ ከተሞች ፀሐይ እና ዝናብ ተፈራርቆበታል፡፡
ሙሐመድ ከወራት የእግር ጉዞ በኋላ መዲና ሲደርስ በርካቶች በመደነቅ ተቀብለውታል፡፡ እርሱም ቢሆን የገጠመው አቀባበል የተለየ ስሜት እንደፈጠረበት ተናግሯል፡፡ ፈረንሳዊው የዑምራ ተጓዥ ሙሐመድ ቦላቢያር፣ አሁን ከቅድስቲቱ መዲና ከተማ ወደ መካ ለመጓዝ በዝግጅት ላይ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












