እስላማዊ የምርምር እና የባህል ማዕከል (Islamic Research and Cultural Center (IRCC) ባዘጋጀው የምርምር አውደ ጥናት ላይ ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 19/2016 የውይይት መርሐ ግብር ተከናወነ። ለግማሽ ቀን በቆየው የውይይት መርሐ ግብር ላይ የተዳሰሰው ጥናት የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የፖለቲካ መድረክ ተሳትፎ የሚዳስስ ነው።
“Participation of Ethiopian Muslims in Politics and Governance: Challenges and the way forward” በተሰኘ ርእስ የተዘጋጀውን ጥናት ማዕከሉ ያሠራው በሕግ ባለሞያው አቶ ዘላለም እሸቱ ደግፌ ነው። በመርሐ ግብሩ ላይ ጥናቱ ቀርቦ ከተለያዩ የሞያ ዘርፎች የተውጣጡ ምሁራን ለጥናቱ መዳበር ግብዐት የሚሆኑ ጉዳዮችን በማንሳት ውይይት አካሄደዋል።
ሚንበር ቲቪ በተመለከተው ጥናት ላይ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የፖለቲካ መድረክ ተሳትፎ ከዐፄ ኃይለሥላሴ የሥልጣን ዘመን አንስቶ እስከ አሁኑ ሥርዐት ድረስ ተዳስሷል። በጥናቱ ላይ የሙስሊም ፖለቲከኞች፣ የሙስሊም የፖለቲካ ፖርቲ አመራሮች፣ የምሁራን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች እና የሙስሊም የፓርላማ አባላት አስተያየት ተካቷል።
እስላማዊ የምርምርና የባህል ማዕከል ይህን ጥናት በማካሄድ ለውይይት ያቀረበው በቀጣይ ተጨማሪ ግብዐቶችን በማካተት የጥናቱን ውጤት ለሚመለከታቸው አካላት በተለያዩ መንገዶች የሚያደርስ መሆኑን የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ አሊ ለ“ሚንበር ቲቪ” ገልፀዋል።
ኢስላማዊ የምርምርና የባህል ማዕከል ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ የሚመለከቱ ከ300 በላይ ጥናቶችን ሠርቷል። ከጥናቶቹ ውስጥ እስላማዊ ኢኮኖሚ እና ፋይናንስ፣ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ የሚዳስሱ ይገኙበታል።
★★★★★
ሚንበር ቲቪን በኢትዮሳት በተሻለ የምስል
ጥራት ለመከታተል
ፍሪኩዌንሲ:- 11545
ሲምቦልሬት:- 45000
ፖላራይዜሽን:- ሆሪዞንታል
★★★★★














