Homeዜናና ወቅታዊዜናጉግል እስራኤልን በቴክኖሎጂ ደግፏል በሚል ተቃውሞ ያሰሙ ሠራተኞቹን ከሥራ አሰናበተ

ጉግል እስራኤልን በቴክኖሎጂ ደግፏል በሚል ተቃውሞ ያሰሙ ሠራተኞቹን ከሥራ አሰናበተ

የአሜሪካው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጉግል፣ እስራኤልን በቴክኖሎጂ አግዟል በሚል ብርቱ ተቃውሞ የሰነዘሩበትን ሠራተኞቹን ከሥራ ማሰናበቱ ታወቀ፡፡ ኩባንያው ለሁለተኛ ጊዜ በወሰደው እርምጃ ያሰናበታቸው ሠራተኞቹ ቁጥር 50 ደርሷል፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የጉግል ሠራተኞች ኒውዮርክ፣ ካሊፎርንያ እና ሲያትል በሚገኙ ቅርንጫፎች አሠሪያቸው ከእስራኤል ጋር እ.አ.አ በ2021 የፈጸመውን የቴክኖሎጂ አቅርቦት ስምምነት ቅጽር ግቢ ውስጥ የመቀመጥ አድማ በማድረግ ተቃውመውታል፡፡

ሠራተኞቹ በዚህ ተቃውሞ የሚሠሩበት ኩባንያ ከእስራኤል ጋር በገባው ስምምነት ቴክኖሎጂ አላግባብ ጥቅም ላይ እንዲውል ተባብሯል በሚል ክስ አሰምተዋል፡፡ ሠራተኞቹ እስራኤል በጋዛ ለምትፈጽመው ጄኖሳይድ ጉግል ተባባሪ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡

ኩባንያው ከእስራኤል ጋር በፈረመው ስምምነት መሠረት ለእስራኤል ጦር የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ሌሎችም ቴክኖሎጂዎችንም በተመለከተ እገዛ ያደርጋል፡፡ በዚህ ስምምነት ሌላኛው የአሜሪካ ኩባንያ አማዞንም ተካቷል፡፡

የተቃውሞው አስተባባሪዎች እንደገለጹት ከሆነ ኩባንያው ቀድሞ 30 ሠራተኞችን ሲያሰናብት፣ በድጋሚ በወሰደው እርምጃ ተጨማሪ 20 ባልደረቦች ከሥራ ተቀንሰዋል፡፡ ጉግል ሠራተኞቹን ለማሰናበቱ ‹የድርጅቴን ሕገ ደንብ ጥሰዋል› የሚል ምክንያት ቢያስቀምጥም፣ የተቃውሞ አስተባባሪዎች ግን በተቃውሞው ላይ ሳይሳተፉ በሥፍራው በመገኘታቸው ብቻ የተባረሩ ባልደረቦቻችን አሉ ሲሉ የአሠሪያቸውን ምክንያት ውድቅ እንዳደረጉት የአልጀዚራ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በአሜሪካ የሚሠራጨው ዘ ኢንተርሴፕት በ2021 ባወጣው መረጃ ጉግል የፊት ገጽታን ጨምሮ ሌሎች ቁስ አካላትን መለየት የሚያስችል የሰው አሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ለእስራኤል አቅርቧል፡፡ ጉዳዩን በአንክሮ የሚከታተሉ አክቲቪስቶች እና ምሁራን የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለጦር አገልግሎት መጠቀም ዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚጻረር መሆንን በመጥቀስ ይቃወሙታል፡፡

እስራኤል ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በጋዛ ላይ በምትሰነዝረው መጠነ ሠፊ ጥቃት እናቶች እና ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 34 ሺሕ ንጹሐን ተቀጥፈዋል፡፡

★★★★★
ሚንበር ቲቪን በኢትዮሳት በተሻለ የምስል
ጥራት ለመከታተል
ፍሪኩዌንሲ:- 11545
ሲምቦልሬት:- 45000
ፖላራይዜሽን:- ሆሪዞንታል
★★★★★

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular