Homeዜናና ወቅታዊዜናየጉለሌ ሙስሊም መካነ መቃብር የቀብር መለያዎችን በቁጥር ብቻ ማድረጉ ቅሬታ አስነሳ

የጉለሌ ሙስሊም መካነ መቃብር የቀብር መለያዎችን በቁጥር ብቻ ማድረጉ ቅሬታ አስነሳ

ከ24 ዓመት ገደማ በኋላ በድጋሚ አገልግሎት መስጠት የጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የጉለሌ ሙስሊም መካነ መቃብር፣ አዲስ በጀመረው አሠራር በሥፍራው የሚያርፉ ምዕመናንን መለያ በቁጥር ብቻ ማድረጉ ቅሬታ ፈጠረ፡፡ ይህ አሠራር ቅሬታ የፈጠረው በሥፍራው ባረፉ ምዕመናን ቤተ ዘመዶች ዘንድ መሆኑን “ሚንበር ቲቪ” ከሰበሰባቸው መረጃዎች መረዳት ችሏል፡፡

መካነ መቃብሩ አገልግሎት መጀመሩ ይፋ የተደረገው መጋቢት 18/2016 ሲሆን፣ ከማግሥቱ መጋቢት 19 ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ “ሚንበር ቲቪ” ማረጋገጥ ችሏል፡፡ በሥፍራው አካላቸው እንዲያርፍ የተደረገ ምዕመናን ማንነታቸው በሥም ሳይጠቀስ በቀብር ሥፍራው አስተዳዳሪዎች የሚሰጥ ቁጥር ሠፍሮባቸዋል፡፡ የሟች ቤተ ዘመዶች በመካነ መቃብሩ ሠራተኞች ከሚተከለው ቁጥር ውጭ ሙሉ ሥም የተጻፈበት ምልክት አልያም ሌሎች መለያዎችን ማድረግ ተከልክለዋል፡፡ ይህን ያደረጉ የሟቾች ቤተ ዘመዶችም ያስቀመጧቸው በሌሎች የሙስሊሞች ቀብር ሥፍራዎች የተለመዱ ያሏቸው የተለያዩ መለያዎች እንዲነሱ መደረጉን ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት የጉለሌ ሙስሊም መካነ መቃብር የቀብር ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዓብዱረሕማን ጁሐር፣ መካነ መቃብሩ እንደገና አገልግሎት ሲጀምር የተከተለው አሠራር ለምዕመናን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በማለም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ ዓብዱረሕማን ጁሐር ይህ የተደረገበት ምክንያት ሁለት መሆኑን ያነሳሉ፤ የሚሰጠው የቁጥር መለያ የሟች ቤተ ዘመዶች ከክፍያ አንስቶ የሚሠጣቸው መሆኑን በመጥቀስ ጥቅሞቹንም አብራርተዋል፡፡ እንደ አቶ ዐብዱረህማን ከሆነ፣ ከሚሰጠው ቁጥር ውጭ ሌሎች መለያዎችን እንዳይደረጉ መከልከሉ በሥፍራው እንዲያርፉ የሚደረጉ ምዕመናን በተያዘላቸው ቅደም ተከተል እንዲስተናገዱ ከማድረጉ በተጨማሪ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የሚያርፉ ምዕመናን እኩል ደረጃ እንዲኖራቸው እንዲሁም በእስልምና ያልተፈቀዱ ልማዶችን ለማስቀረት ነው፡፡ ሰብሳቢው ከዚህ ቀደም በነበረ ሌላ ተመክሮ ቤተ ዘመድ ሳይኖራቸው በመካነ መቃብሮች አካላቸው እንዲያርፉ የሚወሰዱ ምዕመናን በሌሎች ቤተ ዘመድ ባላቸው የተያዘላቸው ተራ (ተቆፍሮ የተዘጋጀላቸው ጉድጓድ) እንደሚወሰድም አስታውሰዋል፡፡

አሠራሩ መተግበሩን ተከትሎ ግርታ የተፈጠረባቸው የሟቾች ቤተ ዘመዶች መኖራቸውን የጠቀሱት ሰብሳቢው፣ ይህ ግርታ ግን በመደበኛ መንገድ የመጣ ሳይሆን በመቃብር ሥፍራው በሚመጡ በኩል ቀርቦ እዚያው አስረድተናቸው ተመልሰዋል ብለዋል፡፡ “ሚንበር ቲቪ” ያናገራቸው ቅሬታ አቅራቢ ግለሰብ በሥፍራው ያረፉ የቤተሰባቸው አባል በቁጥር ብቻ እንዲለዩ መደረጋቸው በቂ አለመሆኑን በመግለጽ በተጨማሪነት ሥም እንዲጻፍ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ በሌሎች የከተማው መካነ መቃብሮች ተመሳሳይ አሠራር እንዳልተመለከቱ የሚገልጹት እኒህ ግለሰብ፣ ቁጥር ከተጻፈ ሥም መካተቱ የሚፈጥረው ችግር ግልጽ አለመደረጉንም አብረው ያነሳሉ፡፡

በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ክፍተኛ ምክር ቤት ስር የሚገኘው ጉለሌ ሙስሊም መካነ መቃብር ያስጀመረውን አዲስ አሠራር በተመለከተ ቁጥርን ብቻ ከያዘው መለያ ባሻገር ከእስልምና አስተምህሮ አንጻር የተገቢነት ጥያቄ የሚያነሱ አሉ፡፡ ለዚህ ምላሽ የሰጡት የጉለሌ ሙስሊም መካነ መቃብር የቀብር ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ አሠራሩን ለመተግበር ከእስልምና አስተምህሮ አንጻር “ከዑለማዎች ጋር መክረንበታል፣ አሁንም እየመከርንበት ነው” ብለዋል፡፡ አቶ ዐብዱረሕማን “እየመከርንበት ነው” ያሉት ጉዳይ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የዑለማ ምክር ቤት ጋር ጭምር የሚደረግ መሆኑን ቢጠቁሙም ከዑለማ ምክር ቤት የተሰጠው ብያኔ ስለመኖሩ የጠቀሱት ነገር የለም፡፡

አሠራሩ ከእስልምና አስተምህሮ አንጻር ያለውን ቦታ ለመረዳት “ሚንበር ቲቪ” ያነጋገራቸው ሸይኽ አሕመድ አወሉ፣ መቃብሮችን ለመለየት ቁጥር ብቻ መጻፍ መሠረት ያለው ነገር አለመሆኑን በመግለጽ፣ በሊቃውንት ዘንድ ለክርክር ሲቀርብ የቆየው ጉዳይ “ሥም መጻፍ ይቻላል ወይስ አይቻልም?” የሚለው መሆኑ አስረድተዋል፡፡ በመቃብር ሥፍራ ላይ ሥም መጻፍ ይቻላል ወይም አይቻልም በሚለው ጉዳይ በአብዛኞቹ ሊቃውንት ዘንድ “የተፈቀደ ነው” በሚል ብያኔ የሚሰጥበት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ የመካነ መቃብሩ ኮሚቴ ሰብሳቢ በሳዑዲ ዐረቢያ ጭምር ይተገበራል ባሉት በዚህ አሠራር፣ በምዕመናን ሥም እንዲካተት የቀረበውን ምክረ ሐሳብ ከዑለማዎች ጋር እንማከርበታለን የሚል ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡

የጉለሌ ሙስሊም መካነ መቃብር ከ1896 ጀምሮ ለአዲስ አበባ ሙስሊሞች ማረፊያነት አገልግሎት ሲሠጥ የቆ ነው፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular