Homeዜናና ወቅታዊዜናዬልን ጨምሮ በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ፍልስጤምን የሚደግፉ ተማሪዎች ሰላማዊ ሠልፍ አካሄዱ

ዬልን ጨምሮ በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ፍልስጤምን የሚደግፉ ተማሪዎች ሰላማዊ ሠልፍ አካሄዱ

የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በሆኑት ዬል፣ ኮሎምቢያ እና ኒውዮርክ ከፍልስጤማዊያን ጎን የቆሙ ተማሪዎች ድጋፋቸውን በሰላማዊ ሠልፍ ማሳየታቸውን ቀጥለዋል። እሑድ የጀመረው የድጋፍ ሠልፍ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አጋር በሆነው በርናርድ ኮሌጅ ቀጥሏል።

ፖሊስ እርምጃ ቢወስድም ሠልፉ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እየተስፋፋ ነው

ሰላማዊ ሠልፉ በሥፋት ከተካሄደባቸው ዩኒቨርሲዎች በተወሰኑት የመማር ማስተማር ሂደት ተቋርጦ ትምህርት በኦንላይን እየተሰጠ ይገኛል። ትናንት ሰኞ የተካሄዱ ሰላማዊ ሠልፎች ኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ በሚገኝበት ማንሃታን እንዲሁም ዬል ዩኒቨርሲቲን አዳርሷል።

ተማሪዎቹ በሰላማዊ ሠልፉ ላይ እስራኤል በፍልስጤማዊያን ላይ የምትፈፅመውን በደል አስተጋብተዋል። ተማሪዎቹ ድምጻቸውን በሰላማዊ መንገድ ቢያስተጋቡም የፀጥታ አካላት ተማሪዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል። በተለይ በዬል ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ሰላማዊ ሠልፍ ስልሳ ሰዎች በቁጥጥር ስር ሲውሉ፣ አርባዎቹ ተማሪዎች ናቸው። ፖሊስ ተማሪዎቹን ለማሰሩ ሕግ ተላልፈው የትራፊክ ፍሰት አስተጓጉለዋል ማለቱን አልጀዚራ ዘግቧል። የኒውዮርክ ከተማ ፖሊስ በተመሳሳይ 108 ሠልፈኞችን ማሰሩን ከንቲባው ኤሪክ አዳምስ ገልፀዋል። ከንቲባው ተማሪዎች ሕግ መተላለፋቸውን ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ በሰላማዊ ሠልፉ ላይ የተሳተፉ ተማሪዎችን ለማገድ ተሳታፊዎችን እያጣሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። ውሳኔያቸውን ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ካደረጉት ውስጥ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ይገኝበታል። ዩኒቨርሲቲዎቹ ይህን ቢሉም ተማሪዎቹ ግን ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ እየገለፁ ይገኛሉ።

ለተማሪዎቹ እገዳ ዩኒቨርሲቲዎቹ ያቀረቡትን ምክንያት በተመለከተ ለአልጀዚራ የተናገሩት በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የመካከለኛ ምሥራቅ እና ኢስላሚክ ስተዲስ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ሄልጋ ጠዊል ሱል የተማሪዎቹ ተቃውሞ ሰላማዊ እንደነበር በመግለጽ የተወሰደውን እርምጃ ተቃውመውታል። ለ20 በኒውዮርክ የተለያዩ ተቃውሞዎች ሲካሄዱ መመልከታቸውን የገለጹት ጠዊል ሱሪ፣ በሠልፈኞች ላይ ተመሳሳይ እርምጃዎች ሲወሰዱ እንዳልተመለከቱ ከቀደሙ ተመክሮዎች ጋር በማነጻጸር አስረድተዋል።

ዬልና ሌሎችም የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ለፍልስጤማዊያን ድጋፍ አደባባይ በወጡ ተማሪዎቻቸው ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ቢያሳውቁም በቀጣይ ቀናት ተቃውሞዎች በካሊፎርንያ፣ በርክሌይ፣ ማሳቹሴትስ፣ ሚቺጋን፣ ኤመርሰን ኮሌጅ እና ቱፍትስ ሊቀጥሉ እንደሚችሉ አስተባባሪዎች እየገለፁ ይገኛሉ።

በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች በአደባባይ ባካሄዱት ሠልፍ ተቃውሞ ያሰሙባት እስራኤል፣ ባለፉት 6 ወራት በጋዛ በሰነዘረችው ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ከ34 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን ተቀጥፈዋል።

★★★★★
ሚንበር ቲቪን በኢትዮሳት በተሻለ የምስል
ጥራት ለመከታተል
ፍሪኩዌንሲ:- 11545
ሲምቦልሬት:- 45000
ፖላራይዜሽን:- ሆሪዞንታል
★★★★★

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular