እሑድ , ذو الحجة 17, 1445
Google search engine
Homeዜናና ወቅታዊዜና12 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ለሐጅ ሥነ ሥርዐት ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ እንደሚጓዙ ታወቀ

12 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ለሐጅ ሥነ ሥርዐት ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ እንደሚጓዙ ታወቀ

የሐጅ ምዝገባ በቀጣይ ሁለት ቀናት ይጠናቀቃል

ለ1445ኛው ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት 12 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ እንደሚጓዙ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) አስታወቀ፡፡ “ሚንበር ቲቪ” ከመጅሊስ ኃላፊዎች ማረጋገጥ እንንደቻለው በተያዘው ዓመት ለሐጅ ክንውን ወደ ሳዑዲ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ምዕመናን ቁጥር ከአምናው በ1 ሺሕ 62 ብልጫ አለው፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በዘንድሮው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ለመታደም የሚፈልጉ ኢትዮጵያውንን ከጥር 25/2016 አንስቶ ሲመዘግብ ቆይቷል፡፡ ምክር ቤቱ በሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ በኩል ለሁለት ወራት ሲያካሄድ የቆየውን ምዝገባ መጋቢት 26/2016 እንደሚያጠናቅቅ ገልጾ የነበረ ቢሆንም በድጋሚ ለጥቂት ቀናት የሚቆይ የጊዜ ማራዘሚያ ሰጥቷል። “ሚንበር ቲቪ”  ይህ የምዝገባ ሒደት በቀጣይ ሁለት ቀናት እንደሚጠናቀቅ ሰምቷል።

ባለፈው ዓመት በተከናወነው የ1444 ዓ.ሂ ዓመታዊው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ 10 ሺሕ 938 ኢትዮጵያውያን ታዳሚ የነበሩ ሲሆን፣ በ1443 ዓ.ሂ 4 ሺሕ ምዕመናን ሥነ ሥርዐቱን ፈጽመዋል።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለሐጅ የምትልካቸው ምዕመናን ቁጥር ባለፉት ዓመታት የተለያየ ቁጥር የተመዘገበበት ነው፡፡ ቁጥሩን በተመለከተ መጋቢት 6/2016 የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ አንስተውታል።

ጉዳዩን ያነሱት የመጅሊስ ዋና ጸሐፊ ሸይኽ ሐሚድ ሙሳ ኢትዮጵያ የሚፈቀድላት ቁጥር ወደ 43 ሺሕ ገደማ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህ ቁጥር “በዶላር እጥረት ምክንያት” እስከ ወደ 12 ሺሕ ዝቅ እንደሚል አስረድተዋል፡፡ ይህ በዶላር እጥረት ምክንያት እንዲቀንስ ተደርጓል የተባለውን የሐጅ ቁጥር አስመልክቶ በመድረኩ ላይ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የሐጅ ቁጥርን ዘንድሮ “በጣም ጨምረናል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ሆኖም ከዋናው ኮታ አንጻር የቁጥሩ ማነስ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ሁኔታ ጋር የሚገናኝ መሆኑን በማንሳት “እንደሌላው ዘርፍ ሁሉ [ለሐጅም] እንቸገራለን” ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሚፈለገው ቁጥር ምዕመናንን ወደ ሐጅ ለመላክ “ብቸኛው መፍትሔ” የኢትዮጵያ “መበልጸግ” እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመት ከዓለማችን ሀገራት በርካታ ምዕመናንን ለሐጅ የምትልከው ኢንዶኔዥያ መሆኗ ታውቋል፡፡ ሀገሪቱ ለ1445 ዓ.ሂ የሐጅ ክንውን 241 ሺሕ ዜጎቿን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ትልካለች፡፡ ዓመታዊውን የሐጅ ሥነ ሥርዐት የምታስተናግደው ሳዑዲ ዐረቢያ ባለፈው ዓመት ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ምዕመናንን ከመላው ዓለም ተቀብላለች፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Google search engine

Most Popular

Recent Comments