ያለፉትን ዓመታት በተቀናቃኝነት የቆዩት የፍልስጤሞቹ የፖለቲካ ኃሎሎች ሐማስ እና ፈትህ በቻይና አደራዳሪነት ንግግር መጀመራቸውን የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቡድኖቹ መሪዎች በአካል ተገናኝተው መወያየታቸውን ትናንት ሰኞ ገልጧል፡፡
ሐማስ እና ፈትህ በተለይ ባለፉት ዓመታት በተቀናቃኝት ቆይተው ከጥቅምት ወር አንስቶ እስራኤል በጋዛ የጀመረችው ዳግም ጥቃት ለንግግር በር ከፍቶላቸዋል፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ሊን ጂያን እንደገለጹት፣ የሁለቱ ቡድኖች መሪዎች ባካሄዱት ውይይት በመሃላቸው ያለውን ልዩነት በንግግር ለመፍታት ፍቃደኝነታቸውን ገልጸዋል፡፡ የሁለቱ ቡድኖች ተወካዮች በቻይና አደራዳሪነት ንግግር ማካሄዳቸው ቢገለጽም የት እንደተገናኙ የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
በቻይና አደራዳሪነት ንግግር መጀመራቸው የተገለጸው ሐማስ እና ፈትህ፣ በተያዘው ዓመት መጀመሪያ በተመሳሳይ የጋራ መንግሥት ስለማቋቋም በሩስያ መዲና ሞስኮ መክረው ነበር፡፡ የአሁኑን ድርድር የመራችው ቻይና በቀጣይም የቡድኖቹን ልዩነት በንግግር ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝት ገልጻለች፡፡
ከሰሞኑ የተካሄደውን ድርድር የመራችው ቻይና የፍልስጤም ችግር የሚፈታው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገርነት ዕውቅና ስታገኝ ነው የሚል አቋም በማራመድ ትተወቃለች፡፡ ሀገሪቱ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመው ጥቃት እንዲቆም የተኩስ አቁም እንዲደረግ ስትወተውት የቆየች ነች፡፡
ሐማስ እና ፈትህ በፍልስጤም ምድር ተጽዕኗቸው የጎላ የፖለቲካ ኃይሎች ናቸው፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በእስራኤል ሀገርነት ላይ የተለያየ አቋም በማራመድ ይታወቃሉ፡፡ ከቡድኖቹ ውስጥ ሐማስ ለእስራኤል ዕውቅና የማይሰጥ ሲሆን፣ ፈትህ በበኩሉ ዕውቅና ይሰጣል፡፡ ቡድኖቹ የፍልስጤም እና እስራኤል ልዩነት በሚፈታበት የትግል ስልት ላይ እንዲሁ ልዩነት አላቸው፡፡












