እሑድ , ذو الحجة 17, 1445
Google search engine
Homeዜናና ወቅታዊዜና200 ገደማ የመብት ተሟጋቾች ፍልስጤምን ደግፈው በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ሠልፍ ከወጡ ተማሪዎች ጎን...

200 ገደማ የመብት ተሟጋቾች ፍልስጤምን ደግፈው በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ሠልፍ ከወጡ ተማሪዎች ጎን ቆሙ

እስራኤል በፍልስጤማዊያን ላይ እየፈጸመች የምትገኘውን ጥቃት በመቃወም በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄደው ሠልፍ ወደ 200 በሚጠጉ በሀገሪቱ በሚንቀሳቀሱ የመብት ተሟጋቾች ድጋፍ አገኘ፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቹ የተካሄዱት ሠልፎች አሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠውን ድጋፍ ጭምር የሚቃወሙ ናቸው፡፡

ፍልስጤምን ደግፈው በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ሠልፍ የወጡ ተማሪዎች በኮሎምቢያ፣ ዬል፣ ቴክሳስ እና ሌሎችም የትምህርት ተቋማት ማሰማት የጀመሩት የተቃውሞ ድምጽ አሁንም ድረስ ቀጥሏል፡፡ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲዎች ቅጽር ግቢ ውስጥ አነስተኛ ድንኳኖችን በመትከል እዚያው ውለው በማደር ለፍልስጤማዊያን ድጋፋቸውን ሲገልጹ ታይተዋል፡፡

ፖሊስ በዩኒቨርሲዎቹ የተካሄዱትን ሠልፎች ለመበተን ሙከራ ያደረገ ቢሆንም ተማሪዎቹ ሠልፉን ቀጥለው በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ተማሪዎች መኖራቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዳንዶቹም በሠልፉ ላይ የተሳተፉ ተማሪዎቻቸውን ማገዳቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡

በአሜሪካ የሚገኙ የመብት ተሟጋቾች ከተማሪዎቹ ጎን የመቆማቸው ዜና የመጣው ፖሊስ እየወሰደ በሚገኘው እርምጃ ተማሪዎቹን ማሰሩ ከተሰማ በኋላ ነው፡፡ 193 የመብት ተሟጋቾቹ በጋራ ባወጡት የአቋም መግለጫ፣ ተማሪዎቹ ሰላማዊ ሠልፍ እያካሄዱ የሚገኙት ‹‹የመቃወም መብታቸውን ተጠቅመው›› መሆኑን በመግለጽ ይህ መብት ሀገሪቱ በደነገገቻቸው ሕጎች የተቀመጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በቀጠለው ሠላማዊ ሠልፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ቢታሰሩም ተቃውሞው ወደ አውሮፓ ተዛምቶ በፈረንሳይ ተካሄዷል፡፡ በእነዚህ ሠልፎች ላይ በተለይ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ተጠይቀዋል፡፡

እስራኤል ባለፉት ወራት በጋዛ በፍልስጤማዊያን ላይ እየፈጸመች በምትገኘው ጥቃት ቢያንስ 34 ሺሕ ንጹሐን ተገድለዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል 13 ሺሕ 800 የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Google search engine

Most Popular

Recent Comments