የረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን ቱርክ ኢራን እና አሜሪካን ለማሸማገል ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ተነግሯል፡፡ ይህን ጥረት ለማቀጠል የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊደን እሑድ እለት ከኢራን፣ ግብጽ እና የአውሮፓ አቻዎቻቸው ጋር በስልክ ውይይት አድርገዋል፡፡
ሚድል ኢስት ዐይ ፊደን በተመሳሳይ በዚሁ ቀን ከአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተነጋግረዋል ብሏል፡፡ እነዚህ ባለሥልጣናት የትራምፕ አስተዳደር የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እና አማቻቸው ጃሬድ ኩሽነር ናቸው፡፡
ከሳዑዲ፣ ከኳታር፣ከኢራቅ እና ከፓኪስታን አቻዎቻቸው ጋር እንዲሁ ተጨማሪ ውይይቶችን በማካሄድ ውጊያውን ለማስቆም የተጀመሩትን ተነሳሽነት በመገምገም ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡ የአንካራን አካሄድ በሚገባ ያውቃሉ የሚባሉ ሰዎች እንደሚሉት፤ ቱርክ ለአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ግፊት እያደረገች ትገኛለች፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በእንዲህ ባለበት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ እለት አሜሪካ ከኢራን ጋር መልካም እና ውጤታማ ውይይት በማድረጓ በኢራን የኃይል ማመንጫዎች እና የኃይል መሠረተ ልማት ላይ የሚደረጉ ወታደራዊ ጥቃቶችን እንዲዘገዩ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት አስቀድመው በሰጧቸው መረጃዎች ከአሜሪካ ጋር የተጀመረ ንግግር እንደሌለ በመግለጽ አስተባብለዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን ወሬውን ገፍተውበት ተስፋ ሰጪ ንግግር መጀመሩን ጠቅሰዋል። በአንጻሩ የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ‘ንግግር ተደርጓል’ መባሉን በማስተባበል የአሜሪካን ፕሬዝዳንት አስተያየት “የፈጠራ ወሬ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።
ስለ ጉዳዩ ሲቢኤስ ኒውስ ዛሬ አንድ የኢራን ባለሥልጣን “በአደራዳሪ በኩል የመነጋገሪያ ነጥቦች ደርሰውናል፤ እየተመለከትናቸው ነው” እንዳሉት ዘግቧል፡፡ የዜና ምንጩ “ይህ ለንግግር ቅድመ ሁኔታ እንጂ ምንም ዓይነት ድርድር እየተካሄደ ስለመሆኑ ወይንም እንደሚኖር አያሳይም” ሲል ዘግቧል። ያልጠራም ቢሆን የድርድር ወሬ መዛመቱን ተከትሎ በእንቅስቃሴው ከአሜሪካ ጋር ኢራን ላይ ጦርነት የከፈተችው እስራኤል ባለሥልጣናት በሒደቱ ደስተኛ አለመሆናቸው ተነግሯል፡፡
አሁን ለሽምግልና ጥረት ጀምራለች የተባለችው ቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊደን የእስራኤልን ሚና በማስመልከት ለጋዜጠኞች ቀደም ብለው ሲናገሩ፤ “እስራኤል ጦርነቱን የማራዘም እና በኢራን ላይ የበለጠ ጉዳት የማድረስ ፖሊሲን ልትከተል ትችላለች” ብለዋል፡፡ አያይዘውም “የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጦርነቱን ውጤት ሊያበላሽ እንደሚችል” ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡ “እንደዚህ ዓይነት አካሄድ ሲኖር ዩናይትድ ስቴትስ የምትወስደው አቋም ወሳኝ ይሆናል” ያሉት ፊደን፤ “ችግሩ እስራኤል ሰላም አለመፈለጓ ነው” ሲሉ ሥጋታቸውን አጋርተዋል፡፡
አንድ የቱርክ ምንጭ ለሚድል ኢስት ዐይ እንደገለጸው፤ አንካራ የእስራኤልን ተፅእኖ ለመቋቋም በድርድር መንገድ አንድ ወጥ ግንባር ለመፍጠር ሙከራ እያደረገች ትገኛለች፡፡ ግጭቱን ለማስቆም ያበረችው ከአውሮፓ፣ ከባህረ ሰላጤ እና ከሌሎች የቀጣናው ተዋናዮች ጋር ባንድነት ነው። በርግጥ የኢራን ዛቻዎች ማጠንጠኛ በባህረ ሰላጤው የኃይል መሠረተ ልማትና ሌሎች ፋብሪካዎች ላይ በመሆኑ በቀጣናው የሚገኙ ሀገሮችን ሥጋት ውስጥ በመክተቱ ሁኔታውን እንደገና እንዲያጤኑት እድል ሰጥቷቸዋል፡፡
ኢራን በአሁኑ ሰዐት ከአሜሪካ የሚቀርብ ማንኛውም የድርድር ጥያቄ ሁለት ጉዳዮችን ማካተት እንደሚኖርበት ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች፡፡ አንደኛው ለወደፊቱ ጥቃት እንዳይሰነዘር ዋስትና ማግኘት ሲሆን፤ ለደረሰባት ኪሳራ ካሣ ማግኘት በሁለተኛነት ሠፍሯል፡፡
እነዚህ ጥረቶች ቢኖሩም የአንካራ ባለሥልጣናት አሁንም ዘላቂ ስምምነት ሊመጣ ይችላል በሚለው ጉዳይ ላይ እምብዛም ተስፋ አለማድረጋቸው ይነገራል፡፡ ባለሥልጣናቱ ጥረታቸውን ቢቀጥሉም፤ በተስፋ እንዳይሞሉ ያደረጋቸው እስራኤል በኢራን ላይ ለረዥም ጊዜ ጥቃት ሳትሰዘር መቆየቷ አጠራጣሪ መሆኑ በቀዳሚነት ተቀምጧል። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን የኒኩለር ማበልጸጓን ሙሉ ለሙሉ እንድታቆም መጠየቃቸውም ሌላኛው ጉዳይ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












