- “[የተነጋገርነው ጦርነት ከመጀመራቸው በፊት ነው]፤ የነዳጅ ነጋዴዎችንና ሕዝቡን ለማሳሳት [የተደረገ] ይመስላል” የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
- የትራምፕ አስተዳደር ለኢራን የድርድር ጥያቄ ቢያቀርብም የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ምላሽ አልሰጡም – የአሜሪካው ድሮፕሳይት ኒውስ
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዓባስ አራቅጂ ከአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር በቀጥታ ንግግር አድርገዋል ሲል ለትራምፕ አስተዳደር ቅርበት ያለው አክሲዮስ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡ ድረ ገጹ ለመረጃው ምንጭ ያደረገው ሥማቸውን ያልጠቀሰውን የአሜሪካ ባለሥልጣን እና ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ ሰዎችን ነው፡፡
ዘገባው በአራቅጂ እና ዊትኮፍ መካከል የተደረገውን ንግግር ዝርዝር ይፋ ባያደርግም፤ ከጦርነቱ መጀመር በኋላ የተደረገ የመጀመርያው ነው ብሎታል፡፡ ይሁን እንጂ የዜናውን መውጣት ተከትሎ አራቅጂ በኤክስ በሰጡት ምላሽ፤ “ከዊትኮፍ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኘሁት ቀጣሪው [ትራምፕን ማለታቸው ነው] በኢራን ላይ ሌላ ሕገ ወጥ ወታደራዊ ጥቃት በመሰንዘር ዲፕሎማሲን ለመግደል ከመወሰኑ በፊት ነው። ከዚህ ውጭ ያለ ነገር የነዳጅ ነጋዴዎችን እና ሕዝቡን ለማሳሳት የታለመ ይመስላል” ብለዋል፡፡
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይህን ምላሽ ከሰጡ በኋላ አክሲዮስ መረጃውን ለሰጡኝ የአሜሪካ ባለሥልጣን ስለ ጉዳዩ በድጋሚ ጠይቄ “አራቅጂ ዋሽተዋል፤ እንዲያውም የመጀመርያውን የጽሑፍ መልእክት የላኩት እርሳቸው ናቸው” እንዳሉት አስነብቧል፡፡ እኒህ ምንጭ አራቅጂ የላኩት የጽሑፍ መልእክት ጦርነቱን ስለመቋጨት የሚያትት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በአንጻሩ ሌላኛው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ድሮፕሳይት ኒውስ፤ የትራምፕ አስተዳደር በአደባባይ በኢራን ላይ በርካታ ዛቻዎች ቢሰነዝርም “ከበስተጀርባ የድርድር ጥያቄ ማቅረቡን” ዘግቧል፡፡ ሁለት የኢራን ባለሥልጣናት ለድሮፕ ሳይት እንደገለጹት፤ የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ባለፈው ሣምንት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዓባስ አራቅጂን ጨምሮ በቴህራን ላሉ ባለሥልጣናት መልዕክቶችን በመላክ “ድርድሩን ለመቀጠል የሚያስችሉ አማራጮችን እየተመለከቱ” ይገኛሉ። ነገር ግን ኢራን ለዊትኮፍ መልስ አልሰጠችም። የኢራን ባለሥልጣናት ለዚሁ የዜና ምንጭ ሀገሪቱ በሦስተኛ ሀገሮች በኩል ከዋይት ሃውስ መልዕክት ተቀብላለች።
በጉዳይ ላይ መረጃ ሰጥተዋል የተባሉት የኢራን ባለሥልጣን ምላሹ ያልተሰጠው ውሳኔውን የማስተላለፍ “ብቸኛ ባለመብት” አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሙጅተባ ኹመይኒ በመሆናቸው ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ “ሚንስትሩ ወይም ሌላ ማንኛውም የኢራን ባለሥልጣን ለባዕዳን ወገን መልዕክት ምላሽ መስጠት የሚችልበት ጉዳይ አይደለም” በማለት አብራርተዋል፡፡
ዋይት ሐውስ በበኩሉ በዚህ ዜና ምንጭ አሜሪካ ለድርድር ጠይቃለች መባሉን አጣጥሎታል፡፡ ዋይት ሐውስ በዚህ ምላሽ ዜናውን ያተመውን ድሮፕ ሳይት ኒውስንም ጭምር “አክራሪ ግራ ዘመም” መገናኛ ብዙኃን መሆኑን በመጥቀስ “ኢራን ውሸት እየፈበረከች ትመግበዋለች፤ የትራምፕ አስተዳደር ግን ሀገሪቱ ከእንግዲህ ወታደራዊ ሥጋት መሆኗ እስኪገታ ድረስ ጥቃቱን ይቀጥላል” ብሏል፡፡
ድርድርን በተመለከት የኢራን ባለሥልጣናት አሁን መደራደር የማይፈለጉት ይህን ማድረግ “አሜሪካ በምታገኘው ፋታ መልሳ ልትደራጅ ትችላለች” በሚል ሥጋት መሆኑን አክሲዮስ አስነብቧል፡፡ በዚሁ ምክኛት ማንኛውም ድርድር የሚደረግ ከሆነ ዘላቂ መሆኑ ላይ ማረጋገጫ ካልተሰጠ ለመጀመር ፍቃደኛ አለመሆናቸው ተገልጿል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












