• “ነዳጅ ቆጥቡ” – የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ
  • 400 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እንለቃለን – ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ
  • ነዳጅ በበርሜል 200 ዶላር ይደርሳል – የኢራን ባለሥልጣን

ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ (አይኢኤ) አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠረውን የነዳጅ ቀውስ ለመግታት አባል ሀገሮቹ 400 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ከመጠባበቂያ ክምችት ለመልቀቅ መስማማታቸውን አስታውቋል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፋቲሕ ቢሮል፤ “በነዳጅ ገበያ የሚገጥመን ተግዳሮት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ስለዚህ የአይኢኤ አባል ሀገሮች በአስቸኳይ የጋራ ርምጃ በመውሰዳቸው በጣም ደስ ብሎኛል” በማለት ውሳኔውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ሀገሮቹ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የተባለውን ነዳጅ የለቀቁት እ.አ.አ በ2022 የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ሲጀመር ነበር፡፡ በወቅቱ የተለቀቀው መጠን 182 ሚሊዮን በርሜል ነው፡፡ የአሁኑ ቁጥር ከዚያን ጊዜው ጋር ሲነጻጸር እጅግ የላቀ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ዓለም አቀፍ የኃይል ኤጀንሲ በ1974 የተቋቋመ በፓሪስ የተመሠረተ ገለልተኛ መንግሥታዊ ድርጅት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ የኃይል ዘርፍ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን፣ ትንታኔዎችን እና መረጃዎችን ይሰጣል፡፡ በኤጀንሲው አባልነት ከተካተቱት መካከል አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ቱርክ ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሀገሮች ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን በርሜል በላይ የመንግሥት የድንገተኛ ጊዜ የነዳጅ ክምችት አላቸው፡፡

ነዳጅ ሊለቅ መሆኑን ያስታወቀው ኤጀንሲው፤ የአደጋ ጊዜ ክምችቱ “ለእያንዳንዱ አባል ሀገር ሁኔታ ተስማሚ በሆነ የጊዜ ገደብ ውስጥ” ለገበያ ይቀርባል ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ኢራን የሆርሙዝ ቦይን መዝጋቷን ለማካካስ በቀን ስንት በርሜል እንደሚለቀቅ ይፋ አለማድረጉን ሚድል ኢስት ዐይ በዘገባው ጠቁሟል፡፡ በአንጻሩ ጃፓን ከሰኞ ጀምሮ 80 ሚሊዮን በርሜል ነዳጃ በተናጠል እንደምትለቅ አስታውቃለች፡፡ ይህ ቁጥር ከ45 ቀናት አቅርቦት ጋር እኩል ነው። ነዳጁ በሚቀጥለው ሣምንት ገበያ ላይ ከዋለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል በሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ከመጠባበቂያ ክምችቱ ላይ 400 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ለመልቀቅ ውሳኔ ቢያሳልፍም፤ ረቡዕ ሌሊት ሦስት የንግድ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ “ምንነቱ ባልታወቀ ተወንጫፊ” መመታታቸው ከተገለጸ በኋላ ዋጋው በድጋሚ አሻቅቧል፡፡ ይህ ጥቃት የተፈጸመው አሜሪካ በአካባቢው በነበሩ በርካታ የኢራን ባሕር ኃይል መርከቦች ላይ ጥቃት ፈጽማ ማውደሟን ካሳወቀች ከሰዓታት በኋላ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የኢራን አብዮታዊ ዘብ ቃል አቀባይ የአሜሪካ እና እስራኤል እንዲሁም አባሪዎቻቸው አሁንም የሆርሙዝን ሰርጥ ለማቋረጥ ሙከራ የሚያደርጉ ከሆነ ኢላማ እንደሚደረጉ በድጋሚ አስጠንቅቀዋል፡፡ “የነዳጅ ዋጋን በሰው ሰራሽ መንገድ ዝቅ ማድረግ አይቻልም” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ነዳጅ በ200 ዶላር በበርሜል ይሸጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል፡፡ አክለውም ዋጋው “በቀጣናው መረጋጋት ላይ የተመሠረተ” መሆኑን በመናገር የቀጣናው “የደኅንነት ዋስትና ማጣት ምንጭ እናንተ ናችሁ” ሲሉ ሀገሮቹን ኮንነዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ሳቢያ በኢትዮጵያም የነዳጅ ዋጋ ጭማር ተደርጓል፡፡ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጭማሪውን ያደረገው ማክሰኞ መጋቢት 1/2018 ከሰዐት በኋላ ነው፡፡ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ረቡዕ እለት በሰጡት መግለጫ ደግሞ በዓለም ላይ የተፈጠረው የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ስለማይታወቅ ኅብረተሰቡ እና ተቋማት ነዳጅን በከፍተኛ ቁጠባ እንዲጠቀሙ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስትሩ በመንግሥት ከተተመነው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ እና የግብይት ሠንሠለት ውጪ ነዳጅ በሚሸጡ ሕገ ወጥ አካላት ላይ የመንግሥት አካላት ርምጃ መውሰድ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትሩ በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ የተደረገው ጭማሪ መንግሥት ነዳጅ ከሚገዛበት የዓለም ገበያ ዋጋ አንጻር እጅግ ዝቅተኛ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

አቶ አሕመድ እንዳሉት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ሊትር የነጭ ናፍጣ ዋጋ 238 ብር ከ13 ሣንቲም ደርሷል፡፡ መንግሥት በሊትር 98 ብር ድጎማ በማድረግ በ139 ብር ከ84 ሣንቲም ለኅብረተሰቡ እንዲቀርብ አድርጓል። በተመሳሳይ ሁኔታ በሊትር 205 ብር ከ74 ሣንቲም በዓለም ገበያ እየተሸጠ ነው ያሉት ቤንዚን፤ መንግሥት በሊትር 73 ብር ከ56 ሣንቲም በመደጎም በ132 ብር ከ18 ሣንቲም ለገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular