የአሜሪካው የሙስሊሞች መብት ተሟጋች “ዘ ካውንስል ኦን አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ” (CAIR)፤ በአንድ ዓመት ውስጥ የቀረቡለትን ቅሬታ ተንተርሶ የሚያዘጋጀውን ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
ድርጅቱ ይፋ ባደረገው ሪፖርት፤ በመላው አሜሪካ በሚገኙ ቢሮዎች በኩል እ.አ.አ በ2025 በሀገር አቀፍ ደረጃ 8 ሺሕ 683 የፀረ ሙስሊም አድልዎ ተግባራት መፈጸማቸውን በቅሬታ ተቀብሏል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት መጠነኛ ጭማሪ ያታየበት ነው፡፡
ድርጅቱ በሪፖርቱ ላይ እንዳሰፈረው፤ ባለፈው ዐመት የሀገሪቱ ሙስሊሞች ሕጋዊ መብቶች “በወረቀት ላይ” ባይለወጡም “በፀረ ሙስሊም ትርክት እና ፖሊሲዎች ምክንያት” መብቶቻቸው ተደፍጥጠዋል፡፡ ይህ ደግሞ ያለ ሃይማኖት ልዩነት ሁሉንም የአሜሪካ ነዋሪዎች ለአደጋ የሚያጋልጥ አዝማሚያ መሆኑን በመግለጽ አስጠንቅቋል፡፡
“ዘ ካውንስል ኦን አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ” የሲቪል መብቶች ሪፖርቱን ማተም የጀመረው በ1996 ነው፡፡ የዘንድሮው ሪፖርት በታሪክ ከፍተኛው የቅሬታ መጠን የተመዘገበበት መሆኑን አስታውቋል፡፡ ለዚህ በርካታ ገፊ ምክንያት መኖሩን የጠቆመው ድርጅቱ፤ የትራምፕ አስተዳደር በዲፓርትመንት ኦፍ ሆምላድ ሴኩሪቲ እና ዲፓርትመንት ኦፍ ኤጁኬሽን የወሰዳቸውን ዘመቻዎች በቀዳሚነት ጠቅሷል፡፡ ዋይት ሀውስ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎችን ለፍልስጤም ድጋፍ በማሳየታቸው ለመቅጣት እንቅስቃሴ ማድረጉንም አስታውሷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዝዳንቱ በግል በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ የሶማሊያ እና አፍጋኒስታን የዘር ግንድ ያላቸውን ሰዎች ጨምሮ በሙስሊም ቡድኖችን በተመለከተ የሰጧቸው መግለጫዎችም አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ገልጿል፡፡
በ2025 ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው “ዘ ካውንስል ኦን አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ”፤ እንደ ድርጅት ባለፈው ዓመት ሰለባ ሆኗል፡፡ ድርጅቱ በቴክሳስ እና ፍሎሪዳ ገዥዎች “የውጭ አሸባሪ ድርጅት” በሚል ቢፈረጅም ውሳኔው በፌዴራል ዳኛ ታግዷል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












