ወርልድ ዊጉር ኮንግረስ በቻይና ምሥራቅ ቱርኪስታን ዢንጂያንግ በሚገኙ ዊጉር (Uyghur) ሙስሊሞች ላይ በረመዳን ወር የተጣለውን አዲስ የጾም ገደብ እና እስራት በመቃወም መግለጫ አውጥቷል። በኮንግረሱ መግለጫ መሠረት፣ በሆታን ግዛት በሚገኙ የተለያዩ መንደሮች ውስጥ የረመዳን ወርን “በምስጢር ጾመዋል” የተባሉ ስድስት ምዕመናን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
ከታሰሩት መካከል ዕድሜያቸው ከ70 ዓመት በላይ የሚገመቱ አምስት አዛውንት ማስጠንቀቂያ እና የፖለቲካ ትምህርት ከተሰጣቸው በኋላ ተለቀዋል። ይሁንና በእስር ላይ የሚገኘው አንድ የ30 ዓመት ወጣት የወንጀል ክስ ሊመሠረትበት ይችላል፡፡ ይህን ተከትሎም ወርልድ ዊጉር ኮንግረስ ድርጊቱን በመቃወም መግለጫው አውጥቷል።
በአሜሪካ ትልቁ የሲቪል መብት ተሟጋች ዘ ካውንስል ኦን አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ በተመሳሳይ ድርጊቱን በማውገዝ የታሰሩ ምዕመናን ተፈትተው ጾማቸውን በሰላም እንዲቀጥሉ ጠይቋል። የአካባቢው ፖሊስ በበኩሉ በረመዳን ወር የክትትል ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብሏል።
እንደ መረጃዎች ከሆነ፤ ፖሊሶች ንጋት ላይ በየቤቱ በመዞር መብራት የበራባቸውን መኖሪያ ቤቶች ይፈትሻሉ። ይህም ሰዎች ሱሁር ለማዘጋጀት መነሳታቸውን ለማረጋገጥ የሚደረግ ነው፡፡ አመሻሽ ላይ የክትትል ሥራው እንደሚቀጥል የገለጸው ፖሊስ፤ በጊዜ የተዘጋ በር ካለ ፍተሻ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
በካሽጋር እና በአክሱ አካባቢዎች የሚገኙ የዊጉር ገበሬዎችን የጾም ፍላጎት ለማዳከም በረመዳን ወር በከባድ የግዳጅ ሥራ እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑን መግለጫው ያመለክታል። የወርልድ ዊጉር ኮንግረስ ፕሬዝዳንት ቱርጉንጃን አላውዱን፣ “ድርጊቱ የዊጉር ሕዝብ በቤቱ ውስጥ እንኳን የመጸለይና የመጾም ነፃነት እንደሌለው የሚያሳይ ነው” ብለዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ብቻ ሳይሆን የቻይናን ሕገ መንግሥት ጭምር የሚጥስ መሆኑንም አስረድተዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በቻይና መንግሥት ላይ ግፊት እንዲያደርግ እና በጾማቸው ምክንያት የታሰሩ ምዕመናን በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የዊጉር ማኅበረሰብ በሰሜን ምዕራብ ቻይና ዢንጂያንግ ከሚገኙት አናሳ ማኅበረሰቦች አንደኛው ነው፡፡ የቱርኪክ ጎሳ አባላት የሆኑት የዊጉር ሙስሊሞች በቻይና ከሚገኙ 20 ሚሊዮን ገደማ ሙስሊሞች ግማሽ ያህሉን ይሸፍናሉ።
የዊጉር ማኅበረሰብ ከሰሜን መካከለኛው እስያ የሚመዘዝ የዘር ግንድ ያለው ከቱርክ ጋር የሚዛመድ ቋንቋ የሚናገር ሕዝብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የዘር ሐረግ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ከአውሮፓውያን፣ ከቻይና፣ ከደቡብ እስያ፣ ከሳይቤሪያና ከመካከለኛው እስያ ጋር ቅይጥ የዘር ሐረግ አለው፡፡ የቻይና መንግሥት የሙስሊሙን ሕዝብ ቁጥር ለመግታት በሚል ዘመቻ የዊጉር ሴቶች እና ሌሎች አናሳ ብሔረሰብ አባላትን ወሊድ መቆጣጠሪያ እንዲጠቀሙ በማስገደድ ክስ ይቀርብበታል። (ሚንበር ቲቪ)












