Homeዜናና ወቅታዊዜናሳዑዲ ዐረቢያ በሣምንት ውስጥ ከ8 ሺሕ በላይ ሕገ ወጥ ነዋሪዎችን ስታባርር፤ በርካታ...

ሳዑዲ ዐረቢያ በሣምንት ውስጥ ከ8 ሺሕ በላይ ሕገ ወጥ ነዋሪዎችን ስታባርር፤ በርካታ ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር አዋለች

የሳዑዲ ዐረቢያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ባለፈው አንድ ሣምንት አካሄድኩት ባለው የተቀናጀ የጸጥታ ዘመቻ፣ የነዋሪነት እና የሥራ ደንቦችን በመጣስ የተገኙ 8 ሺሕ 511 የውጭ ሀገር ዜጎችን ከሀገር ማባረሩን አስታውቋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወደ ሀገሪቱ በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ሊገቡ ነበር ያላቸውን 1 ሺሕ 466 የውጭ ዜጎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ዜጎች መካከል 67 በመቶው ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ 32 በመቶው ደግሞ የየመን ዜጎች ናቸው። ከየካቲት 19 እስከ 25/2018 በተካሄደው ዘመቻ በአጠቃላይ 21 ሺሕ 022 ደንብ ተላላፊዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ሲል የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ከተያዙት ውስጥ 15 ሺሕ 038 የሚሆኑት የነዋሪነት ፍቃድ፣ 3 ሺህ 484 የሚሆኑት የድንበር ጥበቃ እንዲሁም 2 ሺሕ 500 የሚሆኑት ደግሞ የሠራተኛ ህግን በመጣስ የተያዙ ናቸው።

ባለሥልጣናቱ ለሕገ ወጥ ስደተኞች የትራንስፖርት፣ የመጠለያ እና የሥራ ስምሪት በመስጠት የተሳተፉ 15 ሰዎችም መያዛቸውንም ገልጸዋል። የሳዑዲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕገ ወጥ ሰዎችን በማጓጓዝም ሆነ በማስጠለል ለሚሳተፉ ግለሰቦች እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት እና እስከ 1 ሚሊዮን ሪያል የገንዘብ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው በድጋሚ አስጠንቅቋል።

‎በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳዑዲ ዐረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ ያላቸውን 1 ሺህ 635 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው መመለሱን ዛሬ የካቲት 30/2018 ባሠራጨው መረጃ ገልጿል።‎ ‎በሣምንቱ ውስጥ በተደረገ 7 ዙር በረራ ከተመላሾች መካከል አንድ ሴት እና 33 እድሜያቸው ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ይገኙበታል።

በመስከረም 2018 በተጀመረው ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ሥራ እስካሁን 57 ሺሕ 860 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር መመለስ መቻሉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል። የዓለም ዐቀፉ የስደተኞች ድርጅት በኢትዮጵያ የፍልሰተኞች ፍሰት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች የሰዎች እንቅስቃሴን ተመልክቶ ያወጣው የታኅሣሥ ወር ሪፖርት እንደሚያሳየው ከኅዳር ወር መጠነኛ መቀነስ ያሳየ ነው ብሏል። የታኅሣሥ ወር ሪፖርቱ እንደሚያሳየው በወሩ ብቻ 28 ሺህ 33 ዜጎች ከሀገር ወጥተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል 44 ነጥብ 4 በመቶ ወይም 12 ሺህ 448 ዜጎች መዳረሻቸው ሳዑዲ ዐረቢያ እንደሆነ አመልክቷል። በአንጻሩ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ፍልሰተኞች ቁጥር ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፤ አጠቃላይ 11 ሺሕ 435 ፍልሰተኞች ወደ ሀገሪቱ ገብተዋል። በሪፖርቱ መሠረት 61 ነጥብ 9 በመቶውን የያዙት የሱዳን ዜጎች ሲሆኑ ከጅቡቲ፣ ኬንያ እና ሶማሊያም እንዲሁ በርከት ያሉ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አመልክቷል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular