Homeዜናና ወቅታዊዜናየሳዑዲው ድርጅት ወጪውን ለመሸፈን ቃል ገብቶለት የነበረው የንጉሥ ነጃሺ እስላማዊ ማዕከል በኢትዮጵያውያን...

የሳዑዲው ድርጅት ወጪውን ለመሸፈን ቃል ገብቶለት የነበረው የንጉሥ ነጃሺ እስላማዊ ማዕከል በኢትዮጵያውያን ባለሐብቶች እንዲገነባ ውሳኔ ተላለፈ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ የንጉሥ ነጃሺ እስላማዊ ማዕከል ከውጭ ባለሐብቶች እጅ ወጥቶ በኢትዮጵያውያን ባለሐብቶች እንዲገነባ ውሳኔ መተላለፉን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህን የተናገሩት ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 28/2018 በአዲስ አበባ ዐብዮት አደባባይ በተካሄደው ስድስተኛው የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብር ላይ ነው።

በኢትዮጵያውያን ባለሐብቶች ይገነባል የተባለው የንጉሥ ነጃሺ እስላማዊ ማዕከል፤ በሚያዝያ 2012 በመንግሥት በተሰጠ 30 ሺሕ ሜትር ካሬ ቦታ ላይ የሚያርፍ ነው፡፡ የማዕከል ግንባታው ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደሚጠይቅ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ይፋ ያደረገው የባለሞያ የመጀመሪያ ደረጃ ግምት ያመለክታል፡፡

የማዕከሉን ግንባታ የበጀት ምንጭ በተመለከተ ከዚህ ቀደም በሳዑዲ ዐረቢያ መቀመጫውን ያደረገው ዘ ሙስሊም ወርልድ ሊግ በዋና ጸሐፊው ዶክተር ሙሐመድ ዓብዱልከሪም ዒሳ በኩል ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ዶክተር ሙሐመድ ዓብዱልከሪም ዒሳ የግንባታውን በጀት ለመሸፈን ቃል የገቡት ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ነበር፡፡ ይሁንና እስካሁን ድረስ የገቡትን ቃል ተፈጻሚ ስለማድረጋቸው ይፋዊ ማረጋገጫ አልተሰጠም። በዛሬው መርሐ ግብር ላይ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ አልተሰጠበትም።

ቃል የገባውን የግንባታ ወጪ እስካሁን ሳይፈጽም የቀረው ዘ ሙስሊም ወርልድ ሊግ በሳዑዲ ዐረቢያ መካ ከተማ ውስጥ የተመሠረተ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሆኑን በድረ ገጹ ላይ የሠፈረው መረጃ ያመለክታል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular