“የሆርሙዝ መተላለፊያ ተዘግቷል። ማንም ቢሆን ለማቋረጥ ቢሞክር ጀግኖቹ የአብዮታዊ ዘብ ጠባቂዎች እና መደበኛው የባሕር ኃይል መርከቦቹን በእሳት ያደባያል”
የኢራን መንግሥታዊ ጣቢያ እንደዘገበው፤ ይህን የተናገሩት የሀገሪቱ አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ ከፍተኛ አማካሪ ኢብራሂም ጀበሪ ናቸው፡፡ የሆርሙዝ ሰርጥ የምድራችን አንድ አምስተኛው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ያልፍበታል፡፡ በዚህ 40 ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው መተላለፊያ ላይ ማንም እንዳያቋርጥ ኢራን ማስጠንቀቂያ በመስጠቷ ሳቢያ፤ የመርከብ የመድኅን ሽፋን ሰጪ ድርጅቶች ውል እየሰረዙ እንደሚገኙ ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል፡፡
የመተላለፊያው መዘጋት በኮንቴይነር ጫን መርከቦች ላይ ጭምር ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል በዘርፉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ድርጅት ኃላፊዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ይህም የመርከብ ዋጋን ከፍ ያደርገዋል ተብሏል። የኮንቴይነር ተሸካሚው ኦሽን ኔትወርክ ኤክስፕረስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጄረሚ ኒክሰን እንዳሉት፤ ዐሥር በመቶ ገደማ የዓለም ኮንቴይነር ጫኝ መርከቦች በሆርሙዝ መዘጋት ምክንያት መንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡
በዋነኛነት ደግሞ የነዳጅ አቅርቦት ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ ሰኞ እለት በራስ ታኑራ የሚገኘው አራምኮ በመባል የሚጠራው የነዳጅ ማጣሪያ በድሮን ፍንጣሪ የተመታባት የሳዑዲ አረቢያ ትልቁ የሀገር ውስጥ የነዳጅ ማጣሪያ፤ ከጥቃቱ በኋላ ምርቱን ለማቆም ተገዷል።
በተመሳሳይ በመንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደረው የኳታር ኢነርጂ፤ በራስ ላፋን ፋብሪካው ላይ የድሮን ጥቃት ከተሰነዘረበት በኋላ ምርቱን ማቋረጡን ገልጿል። ይህ ፋብሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚቀርበው ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ውስጥ 20 በመቶውን የሚሸፍን ነው። በዚህም የጋዝ ዋጋ እስከ 45 በመቶ ከፍ እንዲል አስገድዷል፡፡ ብሬንት የተባለው ዓለም አቀፉ የናፍጣ ዋጋም በስምንት በመቶ ከፍ ብሎ ሰኞ እለት አንድ በርሜል 78 ነጥብ 40 ዶላር ደርሷል።
የኢራኑ ባለሥልጣን መግለጫ፤ ኢራን የቢፒ ንብረት የሆነውን የባኩ-ትብሊሲ-ጄሃን መተላለፊያን ኢላማ ልታደርግ ትችላለች የሚል ሥጋት ጋርጧል፡፡ ይህ መተላለፊያ ከአዘርባጃን ወደ እስራኤል ድፍድፍ ዘይት ያጓጉዛል። ወደ 30 በመቶ ገደማ የእስራኤል የነዳጅ አቅርቦትም በዚሁ መስመር በኩል የሚፈስ ነው፡፡ ይህ መስመር ከአዘርባጃን በመነሳት በጆርጂያ በማለፍ በቱርክ በኩል ወደ እስራኤል ያደርሳል። ኢራንን ይህ ኢላማ ልታደርገው ትችላለች የሚባለው ከአዘርባጃን በጣም በቅርብ ርቀት ላይ ስለሚገኝ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












