Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችየአሜሪካ እና ኢራን “ገብር - አልገብርም” ትንቅንቅ!

የአሜሪካ እና ኢራን “ገብር – አልገብርም” ትንቅንቅ!

“እኛ በውጭ መንግሥታትም ሆነ ዓለም አቀፍ ባለሥልጣናት አንገደድም፤ ሁሉም ውሳኔያችን በእራሳቸን የሚተላለፍ ነው”


ይህን በ1951 በተባበሩት መንግሥታት ፀጥታው ምክር ቤት ላይ የተናገሩት የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሐመድ ሙሰዲቅ ናቸው፡፡ ሙሰዲቅ ከሰባት ዐሥርት ዓመታት በፊት ይህን ያሉት፤ ሀገራቸው የነዳጅ ኢንዱስትሪዋን (ማለትም በአንግሎ-ኢራን የነዳጅ ኩባንያ የሚተዳደረውን) የራሷ ብቻ ለማድረግ ሕጋዊ መብቷን ለማስከበርና ብሪታንያ ይህን ሉዓላዊ ውሳኔ ለመሻር ዓለም አቀፍ አካላትን ለመጠቀም ያደረገችውን ሙከራ በመቃወም ነው።  “የነዳጅ ቁጥጥርን ብሔራዊ ማድረግ የውስጥ ጉዳይ እና የኢራን ሉዓላዊነት ማሳያ” መሆኑን ያስረዱት ሙሰዲቅ፤ አንድ ሀገር የራሱን የተፈጥሮ ሐብት የመቆጣጠር ውሳኔ ለማሳለፍ ለውጭ አገዛዝ ወይም ለዓለም አቀፍ ጫና መገበር እንደማይኖርበት አስረግጠው ተከራክረዋል።

የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሐመድ ሙሰዲቅ

ብሪታንያ ይህ ከመሆኑ ቀደም ሲል ሀገሪቱ ላይ ጫና ለመፍጠር በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ የባህር ኃይሏን አጠናክራ ሌሎች የነዳጅ ኩባንያዎች የኢራንን ዘይት እንዳይገዙ ጫና ስታደርግ ነበር። የኢራን ጠቅላይ ሚኒስትር ጉዳዩ በብሪታንያ አማካኝነት ወደተባበሩት መንግሥታት ፀጥታው ምክር ቤት ሲሄድ፤ ምክር ቤቱ ኢራንን አቋሟን እንድትለውጥ ለማስገደድ “የጉልበተኛ መጠቀሚያ” ሆኗል ብለዋል፡፡


የያኔው የኢራን ጠቅላይ ሚኒስትር ይህ ንግግር በታሪክ ተመዝግቦ ቢያልፍልም፤ ከሰባት ዐሥርት ዓመታት በኋላ ዳግም ኢራን ተመሳሳይ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች፡፡ በሀገሪቱ ለተከታታይ ሣምንታት የበረታውን ተቃውሞ ተከትሎ አሁን ፍጥጫው ከብሪታንያ  ወደ አሜሪካ ዞሯል፡፡ በሀገሪቱ በተነሳው ተቃውሞ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕየወታቸው አልፏል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እነዚህ ዜጎች መገደላቸውን ተገን በማድረግ ኢራን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሲዝቱ ሰንብተው ዛሬ ረፋድ ላይ ከእስራኤል ጋር በመቀናጀት ወደ ተግባር ለውጠውታል፡፡ ኢራን በአጸፋው በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ላይ ጥቃት ፈጽማለች።


ጉዳዩን የሚከታተሉ በርካታ ታዛቢዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ ቀድሞም ቢሆን አሜሪካ በኢራን ላይ ባላት አቋም ዛሬ ጥቃቱን በሰነዘረችው በእስራኤል ከፍተኛ ተጽዕኖ ስር ወድቃለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የቴህራንን የባሊስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራም እና የኒውክሌር ምርምሯን ሥጋት ለማስወገድ ይፈልጋሉ። እስራኤል በኢራን የአገዛዝ ለውጥን በአደባባይ ስታቀነቅን ቆይታለች፡፡


የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጦር መርከቦች ቡድን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ መሰማራታቸውን ይፋ ያደረጉት ቀደም ብለው ነበር፡፡ አሜሪካ ኢራን ወደ ድርድር የማትመጣ ከሆነ አሜሪካ ርምጃ የምትወስድበት ጊዜ መቃረቡን ፕሬዝዳንት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ ኢራን በተባበሩት መንግሥታት አምባሳደር እና ቋሚ መልዕክተኛዋ አሚር ሳኢድ በኩል የኢራን ለድርጅቱ ዋና ፀሐፊ ባስገባቸው ደብዳቤ፤ የትራምፕ መልዕክት “የኃይል ርምጃ ለመውሰድ ግልጽ እና የማያሻማ” ዛቻ በመሆኑ የዓለም አቀፍ ሕግን የሚቃረን እና የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር የሚጥስ ነው በማለት ድርጅቱ ርምጃ እንዲወስድ ቋሚ መልእክተኛው ጠይቀው ነበር። ኢራን በደብዳቤው “እንዲህ ዓይነቱ ባህርይ ቀጣናዊ ውጥረትን የሚያባብስ፣ ያልታሰበባቸው ክስተቶች እንዲፈጠሩ የሚያደርግ እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኅንነት ቀጥተኛ አደጋ ነው” ብላለች። ዛሬ ከተሰነዘረው ጥቃት በኋላም ቢሆን የተሰተዋለው ይኸው ነው። የኢራን አጸፋ ለአቡ ዳቢ፣ ኩዌት፣ ኳታር እና ባህሬን ተርፏል። የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ በተፈጠረው ውጥረት የአፍሪካ እና ሌሎችም አየር መንገዶች ወደ አካባቢው የሚያደርጓቸውን በረራዎች ሰርዘዋል፡፡


የቱኒዝያ የዘር ግንድ ያላት እንግሊዛዊ የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ተንታኝዋ ሱመያ ጋኑሺ ከጥቂት ሣምንት በፊት በሚድል ኢስት ዐይ ባሳፈረችውና “ምዕራባውያን ለምንድነው የኢራንን ሉዓላዊነት ፈጽሞ የማይቀበሉት?” የሚል ርእስ ባለው ዘለግ ያለ መጣጥፍ እንዳብራራችው፤ አሁን በኢራን ላይ እየተፈጸመ የሚገኘው ጫና ድሮም የነበረ ነው፡፡ ያን ጊዜ ከሰባ ዐመት በፊት የኢራን ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሐመድ ሙሰዲቅ በጸጥታው ምክር ቤት እንዳሉት፤ ሀገሪቱ “በራሷ እንዳትቆምና ለዓለም አቀፍ ጫና እንድትገበር የማስገደድ እንቅስቃሴ ነው”፡፡

የኢራን መሪ ዓሊ ኹመይኒ

ሱመያ እንደምትለው፤ በርግጥ አንድ ሊካድ የማይገባው ጉዳይ አለ፡፡ ኢራናውያን በችግር ውስጥ ናቸው፡፡ በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ለዐሥርተ ዓመታት ከቆየው የኢኮኖሚ ድቀት በኋላ ዝለው ወደ ጎዳናዎች ወጥተዋል፡፡ የመከፋት ስሜታቸው እውነተኛ፤ ቁጣቸውም የማይካድ ነው። ነገር ግን ይህን ያስከተለው ከ1979 ጀምሮ ኢራን በዘመናዊው ታሪክ ውስጥ በጣም ረዥምና ሁሉን አቀፍ የሚባል ማእቀብ ሲጣልባት በመቆየቱ ነው፡፡ በሀብት እና የነዳጅ እገዳ የተጀመረው ማእቀብ፣ በፋይናንስ፣ በኃይል፣ በንግድ፣ በቴክኖሎጂ እና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ሁሉ ያነጣጠረ ሆኗል፡፡


በኢራን ላይ የሆነው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የምዕራባውያንን ጥቅም አደጋ ላይ ሲጥሉ ይችላሉ ተብለው በሚገመቱ መንግሥታት ላይ ሁሉ ሲተገበር የቆየ መሆኑን ተከራክራለች፡፡ እንደ ጸሐፊዋ ከሆነ፤ ምዕራባውያን በሀገራት ላይ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን መፍጠር ሁልጊዜም የሚያደርጉት ነው፡፡ ውስጣዊ ክፍፍሎችን መፍጠርም እንደዚያው፤ በላዩ ላይ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ዘመቻዎችን በመክፈት ተቃዋሚ “አብዮተኞችን” በገንዘብ መደገፍ ይታከልበታል፡፡ እነዚህ ርምጃዎች ካልተሳኩ ደግሞ መፈንቅለ መንግሥት ይደረጋል፤ ወረራውም ይቀጥላል፡፡ ይህ ሁሉ የሚከናወነው “ንጹሐንን ለማዳን” በሚል የዳቦ ሥም ነው፡፡


ኢራን ደግሞ ይህን ሂደት በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ሳይሆን በተግባር ተጋፍጣዋለች፡፡ ሀገሪቱ ይህን በ1953 የተጋፈጠችው በዲሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሐመድ ሙሰዲቅ በኩል  ነበር፡፡ እኒህ መሪ ላይ አሜሪካና እንግሊዝ መፈንቅለ መንግሥት ደግሰው ከሥልጣን እንዲወገዱ አድርገዋል፡፡ ሙሰዲቅ የተወገዱት የሥልጣን ዘመናቸው “በአሰቃቂ ታሪክ የተሞላ” አይደለም፣ በኢራን ነዳጅ ላይ አዛዡ እኛ ብቻ ነን በማለታቸው ነው፡፡ በወቅቱ የኢራንን ነዳጅ የሚዘውረው የአንግሎ-ኢራናዊ የነዳጅ ኩባንያ፣ ከራሷ ሐብት ላይ ለሀገሪቱ የሚሰጠው ትርፍ 16 በመቶ ብቻ ነበር።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

ትራምፕ ጥቃት የሰነዘሩባት ኢራን የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መስራች ናቸው የሚባሉት ሩሆላህ ኹመይኒ በውጭ አገር የተቋቋመው ንጉሣዊ አገዛዝ በመጨረሻ ተገርስሶ፤ የፖለቲካ ነፃነቷን መልሳ ያገኘችበትን ቀን መታሰቢያን 47ኛ ዓመት ያከበረችው  ከሁለት ሣምንት በፊት ነው፡፡ የአሁኑ መሪ ዓሊ ኹመይኒ የተኳቸው የመንፈሥ ሩሁላህ ወደ ሥልጣን የወጡት በ1979 ነበር፡፡ በርግጥ አሜሪካ የድል መታሰቢያ በዐሉ ከመከበሩ አስቀድሞም ለአዲስ ጥቃት ስትገጃጅ ነበር። ለሱመያ ይህ እንዲሁ የተፈጠረ ግጥምጥሞሽ ሳይሆን ኢራን ላይ ለዘመናት ሲንከባለል የቆየው “ገብር አልገብርም” ትግል ተከታይ ክፍል ነው፡፡

ሩሆላህ ኹመይኒ

በዚህ ትንቅንቅ መሃል ለአሜሪካ የጠየቁት ሁሉ እምቢ የማይባሉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ የኢራኑን መሪ ዓሊ ኹመይኒን  ገድለናል የሚል አዋጅ አመሻሹን አስነግረዋል፡፡ ኢራን በበኩሏ ይህ ጥንቅር እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ የሰጠችው ምላሽ የለም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)


ለዚህ ጥንቅር በዋና ምንጭነት ሚድል ኢስት ዐይ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ አልጀዚራ፣ ፕረስ ቲቪ እና ቢቢሲም ተካተዋል፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular