እስራኤል ከመስከረም 2016 ወዲህ በጋዛ ከሰባ ሺሕ በላይ ፍልስጤማውያን ላይ የፈጸመችውን የዘር ፍጅት ለማዳፈን፤ ሃያ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችን ፈንድ በማድረግ አሳሳች ፕሮግራሞችን እንዲሠሩ ማድረጓን አልጀዚራ አጋልጧል፡፡ ጋዜጠኞች በሠሯቸው ፕሮግራሞች አንድም ፍልስጤማዊ ሳያካትቱ ቀርተዋል፡፡
ከዐሥር መገናኛ ብዙኃን የተወከሉ 20 የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎችን የያዘው ቡድን፤ ከአንድ ራድዮ፣ ከሁለት ጋዜጦች፣ ከአንድ የበይነ መረብ ሚዲያ እና ከአምስት ቴሌቪዥኖች የተውጣጡ ፕሮግራም አዘጋጆች ተካተውበታል፡፡ ከሦስቱ ቴሌቪዥኖች መካከል አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ)፣ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኦቢኤን) እና ናሽናል ሚዲያ ኢትዮጵያ (ኤንቢሲ) ይገኙበታል፡፡
በአልጀዚራ “ሊስኒንግ ፖስት” በተሰኘው መሰናዶ ላይ የቀረበውን ፕሮግራም ያዘጋጀው በአፍሪካ ቀንድ ፍልሰተኞች እና ሰብዐዊ መብቶች ላይ በሚያተኩሩ የምርመራ ዘገባዎችን አልጀዚራን ጨምሮ በሚድል ኢስት ዐይ፣ ዘ ጋርዲያን፣ ግሎብ ኤንድ ሚይልና በሌሎችም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በመጻፍ የሚታወቀው ኢትዮ ካናዳዊው ጋዜጠኛ ዘካሪያስ ዘላለም ነው፡፡ ጋዜጠኛው እንደገለጸው፤ ወደ እስራኤል የተጓዘው ቡድን የእስራኤል መንግሥት ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች በመመልመል ሙሉ ወጪያቸውን በመሸፈን ከወሰዳቸው ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ እነዚህ ጋዜጠኞች በአንድ ሣምንት ቆይታቸው የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች፣ ታሪካዊ፣ የሃይማኖት ሥፍራዎችን እንዲሁም እ.አ.አ ኦክቶበር 7/2023 ሐማስ ጥቃት ፈጽሞበታል የተባለበትን ቦታ ጎብኝተዋል፡፡
እስራኤል ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከጎረቤት ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ሞሮኮ፣ ካሜሩን እና ደቡብ አፍሪካ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎችን መልምላ ወስዳለች፡፡ ይሁን እንጂ ምልመላው በአንዳንድ ሀገሮች ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በሌሎች ደግሞ የቲክቶክ ይዘት አዘጋጆች፣ ተወዛዋዦች እና ለተለያዩ ቤተ እምነቶች ቅርበት ያላቸው ሰዎች እንዲጓዙ ተደርጓል፡፡ በአንጻሩ ምልመላው ቀላል ነበር በተባለበት የኢትዮጵያው ስብስብ ውስጥ የሚዲያ ካውንስል ቦርድ አመራር የጉዞው አካል ነበሩ፡፡
በሊስኒንግ ፖስት በተላለፈው ጥንቅር ምልመላው በእስራኤል መንግሥት የታቀደበት መሆኑንና ጉዟቸው ፈንድ መደረጉን ጥቆማ የሰጡት ሐሰን ሎርጋት የተባሉ ደቡብ አፍሪካዊ የፍልስጤም ተቆርቋሪ ናቸው፡፡ ሐሰን ሲናገሩ ለጥርጣሬያቸው መነሻ የሆነው ሰንዴይ ታይምስ፣ ዘ ሲቲዝን እና ቢዝኒውስ በመባል በሚጠሩ ጋዜጦች ላይ የቀረበው ተመሳሳይ ይዘት ያለው ዘገባ ነው፡፡ ሦስቱም መገናኛ ብዙኃን በዘገባቸው የፍልስጤማውያንን ድምጽ ባለማካተታቸው ጉዳዩን ወደ ደቡብ አፍሪካው ፕሬስ ካውንስል በመውሰድ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

የሐሰንን አቤቱታ ያደመጠው ካውንስሉ የጋዜጠኞቹ የእስራኤል ጉዞ ወጪ በማን እንደተሸፈነ ባደረገው ማጣራት ወጪው ሳውዝ አፍሪካን ጄዊሽ ቦርድ ኦፍ ዴፕዩቲስ (South African Jewish Board of Deputies) ድርጅት እንደተሸፈነ ማረጋገጥ ችሏል፡፡ ድርጅቱ ለእስራኤል መንግሥት ቅርበት ያለው ከመሆኑ ባሻገር በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ ለሆኑ የአይሁድ እምነት ተከታዮች መብት እንደሚሟገት የሚገልጽ ነው፡፡ ነገር ግን መገናኛ ብዙኃኑ ባቀረቡት ሪፖርት ይህን ሳይገልጹ ቀርተዋል፡፡
ካውንስሉ በመጨረሻ ባስተላለፈው ውሳኔ አቤቱታው የቀረበባቸው የደቡብ አፍሪካ ጋዜጦች የጋዜጠኝነት አሠራር መርሕን እንዳልተከተሉ በመግለጽ፤ የጉዞ ወጪያቸው በማን እንደተሸፈነ በየድረ ገጻቸው ላይ በማተም ይቅርታ እንዲጠይቁ ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡
ይህንኑ ተከትሎ በአልጀዚራ ይዘታቸው የተመረመሩ ኢትዮጵያውያን የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎችም ጉብኝታቸውን አስመልክቶ ባሰናዷቸው ፕሮግራሞች፤ “ፍልስጤም የሚባል ሕዝብ እንደሌለ” የሚያስመስሉ እንዲሁም ከ70 ሺሕ በላይ በተገደለበት የዘር ፍጅት በሥፍራው “አብዛኛው ሟች በእስራኤል በኩል እንደነበር ተደርጎ” ማቅረባቸው ተጋልጧል፡፡
የፕሮግራም አዘጋጆቹ በሠሩት ዝግጅት ላይ ሙሉ በሙሉ ምርመራ ማድረጉን የገለጸው ጋዜጠኛ ዘካርያስ፤ በቀረቡት ሥራዎች የጋዜጠኝነት ሞያ “የደንብ ጥሰት” እንደተፈጸመ አብራርቷል፡፡ ይህን በማስመልከት የተናገረችው የሰው ሰራሽ ልሕቀት ባለሞያዋ የቀድሞዋ የጉግል ባልደረባ ትምኒት ገብሩ፤ በተለይ በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ የቀረቡ መሰናዶዎችን በማንሳት በእነዚህ ሪፖርቶች አቅራቢዎቹ የእስራኤል የዘር ፍጅት የተፈጸመበትን ጋዛን አሻግረው ቢያሳዩም በሥፍራው የተፈጸመውን ፍጅት የማዳፈንና ከዚያም ሲያልፍ “ፍልስጤማውያን ከእነአካቴው እንደሌሉ” የሚያስመስሉ ዘገባዎችን ማሠራጨታቸውን ገልጻለች፡፡
ዘገባዎቹን በተመለከተ ምላሽ የሰጠው የደቡብ አፍሪካው ሰንዴይ ታይምስ ኤዲተር ማክሁዱ ሰፋራ፤ በጋዜጣው ላይ የጉዞው ፈንድ አድራጊ ያልተጠቀሰው “በመዘንጋት” መሆኑን በመናገር ያስተባበለ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ስለቀረበባቸው ክስ ምላሽ አለመስጠታቸውን የዝግጅቱ አቅራቢ ኒኮላስ ሙኢርሂድ ተናግሯል፡፡
ላንሴት ግሎባል የተሰኘ ተቋም በዚህ ሣምንት ባወጣው ሪፖርት መሠረት በጋዛ ከኦክቶበር 7/2013 ወዲህ በተፈጸመው ጥቃት 75 ሺሕ 200 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












