Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችልዩ ኸበር - የሐጅ “ቪአይፒ” ምዕመናን

ልዩ ኸበር – የሐጅ “ቪአይፒ” ምዕመናን

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ማክሰኞ ጥር 19/2018 በጽሕፈት ቤት በተሰጠው መግለጫ፤ የ1447 ዓ.ሂ የሐጅ ምዝገባ በይፋ መጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ኃላፊዎች እንደተናገሩት፤ በዘንድሮ ሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ለመሣተፍ የተመዘገቡት ምእመናን ቁጥር 5 ሺሕ 269 ነው፡፡ ይህ ቁጥር አምና ከተጓዙት ምእመናን ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ልዩነት የታየበት ነው፡፡ ባለፈው ዐመት የተገለጸው የኢትዮጵያውያን ቁጥር ወደ ስድስት ሺሕ ገደማ ነበር፡፡

በዚህ ዓመት ከመደበኛ በተጨማሪ ምክር ቤቱ “ቪአይፒ” ብሎ የሚጠራውን መስተንግዶ በማዘጋጀት 110 ሑጃጅ ተመዝግበዋል፡፡ የጠቅላይ ምክር ቤቱ የሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ ተጠሪ ዶክተር ሙሐመድ ሷሊህ ከዚህ ቀደም ለጠቅላይ ምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ የተጀመረው “ተመክሮ ለመውሰድ” ነው፡፡ ይህ ምዝገባ በአንድ ሣምንት ውስጥ መጠናቀቁን የተናገሩት ኃላፊው፤ ለእነዚህ ምእመናን የተቀመጠው ኮታ፤ “የአረፋ፣ ሚና እና የሆቴል [መስተንግዶን]” ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ቁጥሩ እንደማይጨምር አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ምክር ቤቱ የቪአይፒ አገልግሎቱን በሁለት ደረጃ ከፍሎታል፡፡ ለቀዳሚው ደረጃ 1 ሚሊዮን 315 ሺሕ ብር ሲያስከፍል፤ ለሁለተኛው 1 ሚሊዮን 15 ሺሕ ብር ተመን አውጥቶለታል፡፡ በዚህ ምድብ የሚገኙ ምእመናን በሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅ ቆይታቸው በተለይ ከማረፊያ ጋር በተገናኘ ልዩ መስተንግዶ ያገኛሉ ተብሏል፡፡ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና የሐጅና ዑምራ አቢይ ኮሚቴ አባል ዐብዱልዐዚዝ አሎ ይህን በተመለከተ በዚህ ሣምንት በሰጡት መግለጫ ሲናገሩ፤ ለሐረም ቀረብ ያለ እንዲሁም ሚና ላይ ለጀመራትም እንዲሁም ቅርብ ቦታ ላይ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡ ሌሎችም አገልግሎቶች “ከክፍያው ጋር የተጣጣሙ ይሆናል” ብለዋል፡፡

ሳዑዲ ዐረቢያ በየሀገሮቹ በመንግሥት ማእቀፍ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የሐጅ አገልግሎት ሰጪዎች ብቻ ፍቃድ የምትሰጥበት የቪአይፒ ሐጅ፤ በአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የሐጅን መንፈሣዊ ዋጋ ሊሸረሽር የሚችል ነው በሚል ሥጋት የሚያጋሩበት ነው፡፡ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ በዘንድሮ ዐመት ቢጀምርም በሌሎች ሀገሮች የቀደመ ታሪክ አለው፡፡ የአገልግሎቱ አቅራቢዎችም የእስልምናን አስተምሕሮ ተመርኩዘን ነው ምእመናንን የምናስተግደው ሲሉ አስተያየቱን ውድቅ ያደርጋሉ፡፡ አገልግሎቱን አቅራቢዎች እንዲያውም ምእመናን ሚና ላይ የተሻለ አገልግሎት በማግኘታቸው፣ በትራንስፖርት ረገድም ረዥም የአውቶቡስ ሰልፍ ቀርቶላቸው መስተናገዳቸውንና ምግብ ያለ እንግልት ባሉበት መቅረቡን እንደሚደሰቱበት በመግለጽ ይከራከራሉ፡፡

በአንዳንድ የቅንጡ ሐጅ መስተንግዶ በድንኳኖች ለምእመናን የሰውነት መታሻ አገልግሎት የሚሰጡ ወንበሮች (massaging chairs) ተካተዋል፡፡ እዚያው ባሉበት እንዲሰግዱም የመስጂድ ንጣፍ ይዘጋጃል፡፡ ምእመናን የምግብ አገልግሎት ለ24 ሰዐት ማግኘት ይችላሉ፡፡ እንደ መደበኛ ሑጃጅ በተለይ በሚና መኝታቸው ከሌሎች ጋር እንዳይገናኝ ይጋረዳል፡፡

ሳዑዲ ዐረቢያ ባለፈው ዐመት ቅንጡውን መስተንግዶ ይበልጥ በማሳደግ በሚና እጅጉን የተቀናጣ (Ultra VIP) መስተንግዶ አስተዋውቃለች፡፡ አገልግሎቱ የተዘጋጀው በሳዑዲያ አየር መንገድ እና አል ቡርጅ በመባል በሚጠራ ዓለም አቀፍ የመስተንግዶ አቅራቢ ድርጅት ነው፡፡ የሐጅ አላፊ እንግዶች በሥነ ሥርዐቱ ሰሞን ብቻ በሚሞላት ሚና፤ ለእነዚህ ምእመናን ቅንጡ የቤት እቃዎች የተሟላላቸው፣ አየር መቆጣጠሪያ የተገጠመላቸው እና የተሻሻሉ የግል ንፅህና መጠበቂያ ሥፍራዎችን ለየብቻ እንዲጠቀሙ ይደረጋል፡፡ በዚህ አገልግሎት የሚጠቀሙት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በእድሜ የገፉ ሑጃጅ እና “ልዩ” ተብለው የተመዘገቡ እንግዶች ናቸው፡፡

በሐጅ ወቅት በርካታ ሺሕ ድንኳኖች የሚተከሉባት ሚና፤ ሥፋቷ ወደ 20 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ገደማ ነው፡፡ በዚህም በአማካይ በሥፍራው የሚገኘው እያንዳንዱ ከሁለት ካሬ ሜትር ያነሰ ይደርሰዋል፡፡ የቅንጡ ሑጃጅ የመኝታ ሥፍራም ይህን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular