በኢራን መዲና ቴሕራን ባለፈው ታኅሣሥ ወር መገባደጃ ላይ በድንገት የፈነዳው ተቃውሞ በሌሎች አካባቢዎች እየተዛመተ መቆሚያ እንደጠፋው አለ፡፡ በወቅቱ ለተቃውሞው መነሻ የነበረው የሀገሪቱ መገበያያ ገንዘብ “ሪያል” ከአሜሪካ ዶላር ጋር ያለው ንጻሬ በከፍተኛ መጠን ዝቅ ማለቱ ነው፡፡ የተቃውሞ ሰልፉ የተጀመረው በቴሕራን ታላቁ ባዛር የሱቅ ባለቤቶች በራቸውን ቆልፈው አደባባይ ሲወጡ ነው፡፡
ዛሬ ማክሰኞ አንድ ዶላር ከአንድ ሚሊዮን በላይ የኢራን “ሪያል” ይገዛል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ 700 ሺሕ ገደማ የነበረ ሲሆን፤ በ2025 አጋማሽ ላይ ደግሞ ዋጋው ወደ 900 ሺሕ ደርሷል። የምጣኔ ሐብት ባለሞያዎች እንደሚሉት፤ ይህ የሀገሪቱ ገንዘብ መዳከም ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን አስከትሏል፡፡ የምግብ ዋጋ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በአማካይ 72 በመቶ ከፍ ብሏል። ዓመታዊው የዋጋ ግሽበት በአሁኑ ወቅት ወደ 40 በመቶ ገደማ ነው።
የኢራን ኢኮኖሚ የታመመው በበርካታ ምክንያቶች መሆኑ ይገለጻል። ሀገሪቱ በሰኔ 2025 ከእስራኤል ጋር የ12 ቀን ጦርነት አድርጋለች፡፡ ይህም በርካታ የኢራን ከተሞችን የመሠረተ ልማት አውድሟል፡፡
ከማእቀብ ጋር የምትነሳው ኢራን፤ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን በቋሚነት ለማንሳት ድምጽ ቢሰጥም፤ በመስከረም 2025 በኑክሌር ፕሮግራም ምክንያት እንደገና ማዕቀብ ተጥሎባታል፡፡ በታኅሣሥ ወር ኢራን ባስተዋወቀች አዲስ ብሔራዊ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት እንዲሁም በምግብ እና መድኃኒት ላይ የሚደረገውን ድጎማ ማንሳቷ የምግብ ዋጋ እንዲንር አድርጓል፡፡
መጀመሪያ ላይ የተቃውሞ መፈክሮች ያተኮሩት በኢኮኖሚ ላይ የነበረ ቢሆንም ኋላ ወደ ገዢዎች ለውጥ ዞሯል፡፡ ተቃውሞው በኢራን ውስጥም ሆነ በሌሎች ሀገሮች ውስጥ በሚኖሩ የኢራን ዲያስፖራ ማኅበረሰቦች ዘንድ በተበታተነ መንገድም ቢሆን ተዛምቷል፡፡ ታኅሣሥ ላይ የተጀመረው ተቃውሞ ከተነሳ ወዲህ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ዋሽንግተን በወታደራዊ መንገድ ጣልቃ ልትገባ እንደምትችል እየዛቱ ይገኛሉ፡፡
የኢራን እስላማዊ አብዮት ዘብ ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ ለተቃውሞ መዛመት የውጭ ሀገሮችን በተለይም አሜሪካ እና እስራኤልን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ ዘቡ በዐሥር የውጭ ሀገሮች የስለላ ኤጀንሲዎች ተቀነባብሯል ያለውን “የሽብርተኛ ሴራ እንዳከሸፈ” አሳውቋል፡፡ ሴራው በሀገሪቱ “ሁከት ለመፍጠር” እና “የኢራንን ማንነት ለማጥፋት” የታለመ ነው ብሏል። ዘቡ “የጠላት ኮማንድ ሩም የተቋቋመው ከ12 ቀናት ጦርነት በኋላ ወዲያውኑ” መሆኑንም ገለጿል፡፡

የአብዮት ዘቡ የስለላ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፤ በእስራኤል አገዛዝ እና በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “በግልፅ ሲደገፍ የሰነበተው አመፅ፤ በሕዝብ መገልገያዎች እና በግለሰቦች ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት” አስከትሏል ብሏል፡፡ የኢራን ባለሥልጣናት የአሜሪካ እና የእስራኤል የስለላ ድርጅቶች በቀጥታ ተሳታፊ እንደነበሩም አረጋግጧል፡፡ በዚህም “የገንዘብ ድጋፍ፣ ሥልጠና እና የመገናኛ ብዙኃን ድጋፍ” በመስጠት በጎዳናዎች ላይ ከሚንቀሳቀሱ “አመጸኞች እና የታጠቁ አሸባሪዎች” ጎን ቆመዋል ሲል አስታውቋል።
በኢራን ላይ ሊደርስ በሚችል ጥቃት ሥጋት እየጨመረ በመምጣቱ በእስራኤልና በአሜሪካ የቀጣናው ድርጊቶች ላይ “በጥብቅ” ክትትል እያካሄደ እንደሚገኝ በመግለጫው አትቷል፡፡ ፕሬስ ቲቪ አንድ የዘቡን ባለሥልጣን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ አሜሪካ በኢራን ላይ ዘመቻ አካሄዳለሁ የሚለው እምነቷ የተመሠረተው በቴህራን አቅም ላይ ባለ “ያልተሟላ ግንዛቤ” ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
ውጥረቱ ማየሉን ተከትሎ የአሜሪካ ቁልፍ ቀጣናዊ አጋር ነች የምትባለዋ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ፤ በየብስ፣ በአየርም ሆነ በውሃ አካል በኢራን ላይ ጥቃት እንዲሰነዘርባት እንደማትፈቅድ አሳውቃለች፡፡ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ “እንዲህ ላለው ወታደራዊ ዘመቻ ምንም ዓይነት የሎጂስቲክስ ድጋፍ” እንደማትሰጥም ገልጿል።
በቀጣናው ከእስራኤል ጋር የሚፋለመው ሂዝቡላህም፤ በኢራን ላይ ጦርነት ቢሰነዘር ገለልተኛ ሆኖ እንደማይቀጥል መሪው ናኢም ቃሲም ተናግረዋል።
በኢራን ላይ ዛቻ የሚሰነዝሩት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው፤ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን እያጠናከረች በመሄዷ ኢራን ከዋሽንግተን ጋር ለመደራደር ፍላጎት እያሳየች ነው ሲሉ ትናንት ሰኞ ለአክስዮስ ጋዜጠኛች ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ የሚገኘው የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የዜና ወኪል (Human Rights Activists News Agency) ሰኞ ዕለት እንዳሳወቀው፤ በኢራን በተካሄዱ ተቃውሞዎች የሟቾች ቁጥር ከ6 ሺሕ ተሻግሯል፡፡ በጠቅላላው 41 ሺሕ 880 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ በተቃውሞው ወቅት ቢያንስ 11 ሺሕ 9 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)
(አልጀዚራ እና አናዶሉ በተጨማሪ ምንጭነት ጥቅም ላይ ውለዋል)












