የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች፤ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን አዘዋውረዋል ያላቸው 28 ሰዎች ላይ ክስ መመሥረቱን አስታውቋል። ክሱን የመሠረተው 1 ሺሕ 800 የሚሆኑ ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ አዘዋውሯል ባላቸው ግለሰቦች ላይ ነው።
በክሱ ላይ የሠፈረው ማብራሪያ፤ ተከሳሾች በሰው ልጅ ለመነገድ በማሰብ የተደራጀ የወንጀል ቡድን በማደራጀት እንዲሁም የቡድኑ አመራር እና አባላት በመሆን ወንጀል ድርጊቱ ላይ መሳተፋቸውን ያስረዳል። ተከሳሾቹ ወንጀሉን ለመፈጸም የተደራጀ የወንጀል ቡድን አደራጅተው በሥራቸው ሌሎች አነስተኛ ሥራ የሚሠሩ ደላሎችን በመመልመል፤ ሰዎች በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ በመሄድ የተሻለ ኑሮ እንደሚኖሩ በማሳመን ሰዎችን ወደ ባሕር ዳር እና ጎንደር ሲልኩ ቆይተዋል። በባሕር ዳር እና ጎንደር አካባቢ ሰዎችን ወደ ሱዳን ድንበር የሚያጓጉዙ ተቀጣሪዎችን በማዘጋጀት ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ከሀገር ሲያስወጡ ቆይተዋል፡፡
በዚህ መንገድ ፍልሠተኞቹን ከኢትዮጵያ ድንበር ካስወጡ በኋላ በዘረጉት የወንጀል መረብ አማካኝነት ወደ ሊቢያ በመውሰድ በመጋዘኖች ሲያጉሩ መቆየታቸውንም ይጠቅሳል። በሊቢያ በሚገኙ ተከሳሾች እና ግብረ አበሮቻቸው በሚያስተዳድሩት መጋዘኖች ውስጥ ሰዎች በሕይወት ለመቆየት ብቻ የሚበቃቸውን ምግብ እንዲያገኙ በማድረግ፤ ወደ ቤተሰቦቻቸዉ ስልክ በመደወል ከፍተኛ ገንዘብ በመጠየቅ ገንዘቡ እስኪከፈል በእዳ ሲይዙም ቆይተዋል ብሏል።
በፍጥነት ገንዘብ መክፈል ላልቻሉ የተበዳይ ቤተሰቦች ተበዳዮችን እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እየደበደቡ እና እያሰቃዩ በተንቀሳቃሽ ምስል በመቅረፅ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመላክ ገንዘብ እንዲከፈል ጫና አድርገዋል ሲል ክሱ ያትታል። አክሎም ገንዘቡ ከተገኘ በኋላ ለመክፈል ፍቃደኛ ሲሆኑም፤ በቁጥጥር ስር ውለው ክስ የቀረበባቸው ስምንት ተከሳሾችን ጨምሮ በሌሎች ግብረ አበሮቻቸው የባንክ ሂሳብ በመጠቀም ገንዘብ አሰባስበዋል ሲል አብራርቷል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ስምንት ገንዘብ ሰብሳቢዎች ብቻ ከ2 ነጥብ 16 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰባቸውን የክስ መዝገቡ ላይ ሰፍሯል።
በዚህም ተከሳሾቹ በአጠቃላይ 1 ሺህ 800 ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ አዘዋውረዋል የሁለት ሰው ሕይወት ማለፉ መረጋገጡንም ዐቃቤ ሕግ ገልጿል። በድርጊቱ ሁለት ሰዎች በድብደባ ምክንያት ለበሽታ መዳረጋቸውን ሲገለጽ፤ 15 ግለሰቦች የደረሱበት አለመታወቁን ክሱ ያስረዳል፡፡ በዚህም ዐቃቤ ሕግ በከባድ ግለሰቦቹ ላይ ሕገ ወጥ ሐዋላ በመሥራት ሐብት የማሸሽ ወንጀል ክስ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












