የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና ኤፍ.ኤስ.ዲ. ኢትዮጵያ፤ “ሱኩክ” በመባል የሚጠራውን እስላማዊ ቦንድ ወደ ተግባር ለማስገባት ያስችላል የተባለ ውይይት ማካሄዳቸው ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባወጣው መረጃ እንዳሳወቀው፤ አገልግሎቱን ወደ ሥራ ለማስገባት “ረዥም ጊዜ ወስዶ ሲያጠና እንዲሁም በተለያዩ ሂደቶች ውስጥ እንዲያልፍ” አድርጓል፡፡
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ካሣ (ዶ/ር) እና የኤፍ.ኤስ.ዲ. ኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሒክመት ዓብዱላህ እንዲሁም ከሁለቱም ተቋማት የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡ “ተደራሽ፣ አካታች እና ዘላቂ የፋይናንስ ገበያዎችን በማሳደግ የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት” ይሠራል የተባለው ኤፍ.ኤስ.ዲ. ኢትዮጵያ ተወካዮች፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለሚሠራቸው ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎቶች የቴክኒክ እና የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ እና አብሮ ለመሥራት በሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
ውይይቱን ማካሄዱን የገለጸው ብቸኛው የሀገሪቱ የፖሊሲ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፤ የመጀመርያውን ከወለድ ነፃ ቦንድ “ሱኩክ” ሥራ ላይ በማዋል ለኢንቨስትመንት የሚሆን ሐብት ለማሰባሰብ መዘጋጀቱን የገለጸው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ባስጀመረበት መስከረም/2016 ነበር፡፡
በዓለማችን በርካታ ሀገሮች ውስጥ ስኬታማ መሆኑ በተረጋገጠው እስላማዊ ፋይናንስ፤ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እ.አ.አ በ2023-2024 ሦስቱ የአፍሪካ ትልልቅ ኢኮኖሚዎች በሚባሉት ማለትም ናይጄሪያ፣ ግብፅ እና ደቡብ አፍሪካ በሱኩክ አማካኝነት 3 ነጥብ 045 ቢሊዮን ዶላር ማሰብሰብ ያስቻለ መሆኑን ይፋዊ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያ ከሸሪዓ ጋር ተስማሚ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ አራት ባንኮች በሥራ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመርያው ወለድ አልባ የኢንሹራንስ አገልግሎት ሰጪ “አማና ኢንሹራንስ”፤ በቅርቡ ሥራ የመጀመር ዕቅድ እንዳለው መሥራቾች ከዚህ ቀደም ተናግረዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












