Homeዜናና ወቅታዊዜናአሕመዲይ መስጂድ (እርግበር) መስጅድ

አሕመዲይ መስጂድ (እርግበር) መስጅድ

#ኸበር፡ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ በሚያዝያ 2014 ሙስሊሞች ላይ ያነጣጠር ጥቃት መድረሱ የሚታወስ ነው፡፡ የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በወቅቱ እንደገለፀው፤ በጎንደር ሙስሊም መካነ መቃብር ቦታ ላይ የቀብር ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ሳለ ለቀብር በወጡ ሙስሊሞች ላይ በቡድን እና በነፍስ ወከፍ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል፡፡ ጥቃቱ የተሰነዘረው “አስቀድመው በተዘጋጁ መሣሪያዎች” መሆኑንም ገልጿል፡፡ የወቅቱ የከፍተኛ ምክር ቤት ኃላፊዎች ጥቃት አድራሾቹ፤ “አንድ ሀገር፣ አንድ ሃይማኖት’ የሚሉ ፅንፈኛ አክራሪዎች” ናቸው ብለው ነበር፡፡  

በዚህ ጥቃት ከ20 በላይ ምእመናን ሸሒድ ሆነዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል፡፡ በርካታ ሴቶችም ተደፍረዋል፡፡ በምእመናን ላይ ከደረሰው ጉዳት ባለፈ መስጂዶች ጥቃት ተፈጽሞባቸው ቅዱስ ቁርአን ተቃጥሏል፡፡ በርካታ የጎንደር ሙስሊሞች የንግድ ሱቆችም የዘረፋና የቃጠሎ ኢላማ ተደርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ደግሞ፤ በከተማው በሙስሊሞች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት “በአክራሪ ኦርቶዶክስ ክርስትያኖች በተጠና እና በታቀደበት” መንገድ የተሰነዘረ ነው ብሎት ነበር፡፡ ድርጊቱን ተከትሎ የፍትሕ ሚኒስቴር በነሐሴ ወር 2014 ባቀረበው የሪፖርት ውጤት፤ በጥቃቱ 20 ሰዎች መገደላቸውን የገለጸ ሲሆን፤ 11 መስጅዶች መጎዳታቸውንና ከፍተኛ ንብረት መውደሙንም አረጋግጧል፡፡ ይሁን እንጂ ጥቃቱን ባደረሱ አጥፊዎች ላይ እስካሁን ድረስ በሕግ ተጠያቂነት ስለመስፈኑ በይፋ አልተገለጸም፡፡

በጥቃቱ ውድመት ከደረሰባቸው መስጂዶች መካከል አሕመዲይ መስጂድ (እርግበር) አንደኛው ነበር፡፡ “ሚንበር ቲቪ” ከከተማዋ ነዋሪ ማረጋገጥ እንደቻለው፤ መስጅዱ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት መስኮቶችን ጨምሮ የተለያዩ ውድመቶች አስተናግዷል፡፡ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ በምእመናን ትብብር ይዞታውን ቀድሞ ወደነበረበት መመለስ ተችሏል፡፡ በግቢው ውስጥ የተጀመረው ማስፋፊያ ግንባታ ቀጥሏል፡፡

ይህን መስጅድ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ጎብኝተውታል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኀበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዳንኤል ክብረት መገኘታቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ላይ ያጋሩት ተንቀሳቃሽ ምስል ያመለክታል፡፡ አቶ ተመስገን ጥር 13/2018 ከምስሉ ጋር ባጋሩት ጽሑፍ፤ “ሕዝብን ማጋጨት ዓላማቸው በሆኑ አካላት የተጎዳውን መስጂድ ሕዝብን ማስተሣሠር ዓላማቸው የሆኑ ወገኖች መልሰው ገንብተውታል” ብለዋል፡፡ አክለውም “ሁላችንም ደኅና ካልሆንን በተናጠል ደኅና ልንሆን አንችልም፤ ስለዚህም እኛ ደኅና እንድንሆን የሌሎችን ደኅንነት ማረጋገጥ ይገባናል” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

የፎቶ ቅጂ፡ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የኤክስ ገጽ

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular