የሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ጨምሮ በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ሊገቡ ነበር ያሏቸውን 1 ሺሕ 491 ፍልሰተኞችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡ በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል 59 በመቶው ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ የመናውያን መሆናቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም የሳዑዲ መንግሥት ለአንድ ሣምንት አካሄድኩት ባለው ፍተሻ 14 ሺሕ 621 ስደተኞች ከሀገሪቱ መባረራቸውን ገልፍ ኒውስ ዘግቧል፡፡ ፍተሻው የተደረገው በሀገሪቱ የተጀመረው ሕገ ወጥ ነዋሪዎችና ሠራተኞችን እንዲሁም የድንበር ጥሰቶችን ለመቆጣጠር ነው ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ የመኖሪያ፣ የሠራተኛ እና የድንበር ደኅንነት ሕጎችን ጥሰው ተገኝተዋል ያላቸውን ከ18 ሺህ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሳዑዲ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ሌሎች 19 ሺሕ 835 ሕግ ተላልፈዋል የተባሉ ሰዎች የጉዞ ሰነድ እንዲያገኙ ወደየሀገራቸው ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች ተመርተዋል።
የሳዑዲ ዐረቢያ መንግሥት ለማንኛውም ሕገ ወጥ ስደተኛ መጠለያ፣ መጓጓዣ ወይም የሥራ ዕድል የሚሰጡ ግለሰቦች እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና እስከ 1 ሚሊዮን ሪያል በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚጣል በድጋሚ አስጠንቅቋል። በተጨማሪም 27 ሺሕ 518 የውጭ ሀገር ዜጎች (25 ሺሕ 552 ወንዶች እና 1 ሺሕ 966 ሴቶች) ሕጋዊ ርምጃ ተወስዶባቸው የመባረር ሂደታቸውን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ማክሰኞ ጥር 12/2018 ባወጣው መረጃ፤ በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ 3 ሺሕ 142 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሱን ገልጿል። በሣምንቱ ውስጥ በተደረገ 11 ዙር በረራዎች ከተመለሱት ውስጥ 2 ሺሕ 980 ወንዶች እና 141 ሴቶችን ጨምሮ 21 ህፃናት ይገኙበታል።
የዓለም የፍልሰተኞች ድርጅት በቅርቡ በየመን ባወጣው ሪፖርት፤ ወደ የመን ከፈለሱ 21 ሺሕ በላይ ሰዎች መካከል 98 በመቶ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አስታውቆ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ 72 በመቶው መዳረሻቸውን ሳዑዲ ዐረቢያ ያደረጉ መሆናቸውን በሪፖርቱ ሠፍሯል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












