በዓለም አቀፉ የሐላል ገበያ፤ የሐላል ማሸጊያዎች ገበያ (Halal Packaging Market) መጠን እ.አ.አ በ2024 ከነበረበት 300.41 ቢሊዮን ዶላር፤ ከስምንት ዓመት በኋላ በ2032 516.16 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይጠበቃል ሲል አዲስ ሪፖርት አመልክቷል። ገበያው ለዓለም አቀፍ የሐላል ኢኮኖሚ ወሳኝ ግብዐት እየሆነ መጥቷል ተብሏል።
በሐላል ማሸጊያ የማሸጊያ ቁሳቁሶች በሒደቱ እስላማዊ መርሆዎች መሟላታቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የምርት ሰንሰለቱ በሙሉ ሐላል ባልሆኑ ንጥረ ነገሮች እንዳይበከል ማረጋገጫ ማግኘት ይኖርበታል። ይህ ሒደት በሐላል የምስክር ወረቀት የተረጋገጡ ምግቦች፣ መጠጦች፣ መድኃኒቶች፣ መዋቢያዎች እና የግል እንክብካቤ መጠበቂያ ምርቶች ንጹሕ ሆነው እንዲቆዩ ለማድረግ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሙስሊሞች የሕዝብ ቁጥር ማደግና በሐላል መሥፈርቶች ላይ ግንዛቤ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ለሀላል ተስማሚ የማሸጊያ መፍትሄዎች ፍላጎት ያለማቋረጥ እያደገ ይገኛል። አምራቾች እና የምርት ሥም ባለቤቶች የምሥክር ወረቀት መስፈርቶችን ለማሟላት፣ የሸማቾችን አመኔታ ለማሳደግ እና ትርፋማ ወደሆኑ የሐላላ ገበያዎች ለመድረስ ሐላል ማሸጊያ አማራጮችን መጠቀም መጀመራቸው ይነገራል፡፡
ከሀገሮቹ መካከል የእስያዋ ማሌዥያ የላቀ የሐላል የምሥክር ወረቀት ሥነ ምሕዳሯን በማሳደግ የመጀመርያ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በዘርፉ በሀገር ውስጥ ፍጆታ እና የቁጥጥር ድጋፍ በማድረግ ኢንዶኔዥያ ተጠቃሽ ነች፡፡ ሳዑዲ ዐረቢያ ደግሞ በምግብ እና በመድኃኒት የመካከለኛውን ምሥራቅ ገበያ ትመራለች፡፡ በሐላል ንግድ እና የሎጂስቲክስ ማዕከልነት ተጠቃሿ የተባበሩት ዐረብ ኤሚሬቶች ሆናለች፡፡ ቱርክ በሐላል ዘርፍ በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ድልድይ ሆና እያገለገለች መሆኗ ይጠቀሳል፡፡
ዓለም አቀፉ የሐላል ኢንዱስትሪ ወቅታዊ የገበያ ዋጋ ከ2028 በፊት 10 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። በአሁኑ ወቅት ከዓለም የሕዝብ ቁጥር የሙስሊሞች ቁጥር አንድ አራተኛ የሚገመት ነው፡፡ ይህ ቁጥር እ.አ.አ በ2050 ወደ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን እንደሚደርስ የሚገመት ሲሆን፤ በየጊዜው መጨመሩ ለገበያው እምቅ አቅም መሆኑንም የዘርፉ ባለሞያዎች ይገልጻሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












