Homeዜናና ወቅታዊዜናየቱርኩ ፕሬዝዳንት ትራምፕና ኢራንን በስልክ ለማደራደር ጥያቄ አቀረቡ

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ትራምፕና ኢራንን በስልክ ለማደራደር ጥያቄ አቀረቡ

የቱርክ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን፤ ለአሜሪካ አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን መሪ ጋር በቴሌ ኮንፈረንስ ለማገናኘት ጥያቄ ማቅረባቸውን ከባለሥልጣናት ሰምቻለሁ ብሎ ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል፡፡ በዘገባው መሠረት፤ ፕሬዝዳንቱ መሪዎቹን በስልክ ለማገናኘት ያቀዱት በቀጣይ ቀናት ነው፡፡

ይህ የስልክ አማራጭ የመጣው ባለፈው ሰኞ ኤርዶጋን እና ትራምፕ የስልክ ልውውጥ ማድረጋቸው ከተሰማ በኋላ ነው፡፡ በዚሁ ቆይታ ወቅት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ለአሜሪካ መሪ “ከኃይል አማራጭ ይልቅ” ዲፕሎማሲን እንዲያስቀድሙ ሞግተዋቸዋል፡፡ በአደባባይ ንግግሮች ኤርዶጋንን “በጣም ጥሩ ሰው ነው፤ እወደዋለሁ” ሲሉ የሚደመጡት ትራምፕ ለቀረበው አማራጭ “አዎንታዊ” ምላሽ ሰጥተዋል ተብሏል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸውን ተከትሎ የኢራን ፕሬዝዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን ምላሽ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡

ስለ ጉዳይ እናውቃለን የሚሉ የአንካራ ውስጥ አዋቂዎች፤ በዚህ ሣምንት ኢስታንቡልን የሚጎበኙት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አባስ አራቅጂ የቴህራንን ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አራቅጂ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ለማድረግ ጁምዐ ቱርክ ይገባሉ።

ይሁን እንጂ የውይይት አማራጭ መቅረቡ ተጋርጧል የሚባለውን የአሜሪካ እና ኢራን ወታደራዊ ፍጥጫን ማስወገዱ አልያም አለማስወገዱ ላይ ርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል ዘገባው ጠቁሟል፡፡

ከጥቂት ሣምንታት በፊት በኢራን የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን ላይ ጥቃት ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ሲዝቱ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ገፃቸው ዩኤስኤስ አብርሀም ሊንከን በመባል የሚጠራው ግዙፍ የጦር መከርባቸው እና ሌሎች ኃይሎች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ መሰማራታቸውን ገልጸዋል፡፡ አስፈላጊ ሲሆን “በፍጥነት እና በአደገኛ ሁኔታ” የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም ዝግጁ ናቸው ብለዋል፡፡

ምንም እንኳ ይህ የአውሮፕላን ማረፊያ ያለው መርከብ ትክክለኛ አድራሻውን ከአንድ ሣምንት በላይ ይፋ ባያደርግም አንድ አውሮፕላን ኦማን አካባቢ ሲያርፍ ፍላይራዳር24 በተባለው የአውሮፕላኖች መከታተያ ድረ ገፅ በመታየቱ መርከቡ ኦማን አካባቢ እንዳለ እንደሚገመት የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡ ዩኤስኤስ አብርሀም ሊንከን፤ የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ከያዙ የአሜሪካ የጦር መርከቦች አንዱ ሲሆን የአሜሪካ ባሕር ኃይል “የዓለማችን ትልቁ የጦር መርከብ” ሲል እንደሚጠራው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

እንደ ዘገባዎች ከሆነ፤ አሜሪካ በኢራን ላይ ባላት አቋም በእስራኤል ከፍተኛ ተጽዕኖ ስር ወድቃለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የቴህራንን የባሊስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራም እና የኒውክሌር ምርምሯን ሥጋት ለማስወገድ ይፈልጋሉ።

በተጽእኖ ስር ወድቀዋል የሚባሉት ትራምፕ፤ ሀገራቸው በኢራን ጉዳይ “እንደ ቬንዙዌላ ሁሉ፣ አስፈላጊ ከሆነም በፍጥነት ተልእኮዋን መወጣት ትችላለች” ሲሉ በዚህ ሣምንት ጽፈዋል፡፡

ድርድርን በተመለከተ በዛሬው እለት በሲኤንኤን በታተመ ቃለ ምልልስ ላይ ያነሱት የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሙሐመድ ባከር ካሊባፍ፤ ቴህራን የውይይት እና የዲፕሎማሲ መርህን እንደማትቃወም በመግለጽ፤ ድርድሩ እውነተኛ፣ ሚዛናዊና እርስ በርስ መከባበር ላይ የተመሠረተ መሆን እንደሚኖርበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ አክለውም በጦርነት ጥላ ስር የሚደረጉ ድርድሮች ውጥረቶችን እና አለመረጋጋትን እንደሚያባብስ በመጠቆም፤ ኢራን በዓለም አቀፍ ሕጎች እና መመሪያዎች መሠረት እውነተኛ ንግግሮችን ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለሁ ብለዋል። በዚህ ቆይታ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በጦርነት ሥጋት የራሳቸውን የፖለቲካ አመለካከት ለመጫን እንደሚፈልጉ አረጋግጠዋል ሲሉ አካሄዳቸውን ተችተዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular