Homeዜናና ወቅታዊዜናሳዑዲ ዐረቢያ 1 ሺሕ 800 የውጭ ሀገር የዑምራ የጉዞ ወኪሎች ላይ እገዳ...

ሳዑዲ ዐረቢያ 1 ሺሕ 800 የውጭ ሀገር የዑምራ የጉዞ ወኪሎች ላይ እገዳ ጣለች

የሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅና ዑምራ ሚኒስቴር፤ 1 ሺሕ 800 የውጭ ሀገሮች የዑምራ የጉዞ ወኪሎችን ማገዱን አዲስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ሚኒስቴሩ ውሉን ያቋረጠው “ጥሰት ፈጽመዋል” ያላቸውን ወኪሎች ነው። እነዚህ ወኪሎች የታገዱት በዑምራ ዘርፍ ከሚሠሩ አጠቃላይ 5 ሺሕ 800 መካከል ተለይተው ነው፡፡ ይህ ቁጥር የጠቅላላውን አንድ ሦስተኛው ድርሻ ይሸፍናል፡፡

የሐጅና ዑምራ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ እገዳው የተጣለው ወኪሎቹ ላይ “በተደረገ ግምገማ” የአፈጻጸም እና የአገልግሎት ጥራት ጉድለት በመታየቱ ነው። ሳዑዲ ጋዜጣ እንደዘገበው፤ የታገዱት የዑምራ የጉዞ ወኪሎች ከየትኞች የዓለም ሀገሮች እንደሆኑ በዝርዝር ባይጠቀስም የተገኘባቸውን ጉድለት እንዲያስተካሉ የ10 ቀናት ገደብ ተቀምጧል። በተሰጠው ቀን ውስጥ ያላስተካከለ የጉዞ ወኪል ላይ ሕጋዊ ርምጃ ይወሰድበታል፡፡

እገዳው ተግባራዊ የሚደረገው አዳዲስ ቪዛዎች ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በዑምራ ሥነ ሥርዐት ላይ የሚሳተፉ ምዕመናን መብት መጠበቅ እና የአገልግሎት ቀጣይነት ማረጋገጥ በሁሉም የቁጥጥር እርምጃዎች ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር መሆኑን አጽንኦት የሰጠው ሚኒስቴሩ፤ ርምጃው የተወሰደው ኤጀንሲዎች የአገልግሎት አሰጣጣቸውን እንዲያሻሽሉና በተቀመጡ መስፈርቶች መሠረት እንዲሠሩ ለማድረግ እንደሆነ አመልክቷል። እገዳው ቢጣልም ሕጋዊ ቪዛ ያላቸው እና ቀድመው ቦታ ለተያዘላቸው ምዕመናን አገልግሎቱ እንደማይቋረጥ ተገልጿል።

የሐጅና ዑምራ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ገሳን አልንዋይሚ፤ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያሉትን ጉድለቶች ላስተካከለ ወኪል ውሉ እንደሚመለስለት በመጠቆም፤ ይህን ማድረግ ባልቻለ ማንኛውም ኤጀንሲ ላይ “የቁጥጥር ርምጃም ተግባራዊ እንደሚደረግ” አረጋግጠዋል፡፡

“ሚንበር ቲቪ” ከኢትዮጵያ ሐጅ አና ዑምራ አገልግሎት ሰጪዎች ማኀበር ባገኘው መረጃ መሠረት፤ ከ140 በላይ ድርጅቶች በስሩ ተመዝግበው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል እግዱ የተጣለባቸው ስለመኖራቸው ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular