በቴክኖሎጂ ዘርፍ ግዙፍ ሥም ካላቸው ትዊተር እና ፒንትረስት ምሥረታ ጀርባ ያሉት ሁለቱ እውቅ የቴክኖሎጂ ሰዎች፤ በማኅበራዊ ሚዲያ ደረሰ ለሚሉት “አስፈሪ ውድመት” ማርከሻ እንዲሆን የተዘጋጀ መተግበሪያ አቅርበዋል። አዲሱን መተግበሪያ ያስተዋወቁት የትዊተር (አሁን ኤክስ በመባል የሚጠራው) መሥራች ቢዝ ስቶን እና መረጃን በዲጂታል ፒንቦርዶች መልክ የሚያቀርበው ፒንትረስት መሥራች ኢቫን ሻርፕ ናቸው፡፡
ፋይናንሻል ታይምስ እንደዘገበው፤ ሁለቱ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ለአዲሱ ጅምር ሥራቸው 29 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አሰባስበዋል፡፡ “ቴንግል” የተሰኘው መተግበሪያ፤ ተጠቃሚዎች የግል “ሕልማቸውንና መድረስ የሚፈልጉበትን ግብ ከጓደኞቻቸው ጋር እንዲጋሩ”፣ “እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ” እና “ስኬትን” የሚያበረታታ ነው ተብሏል፡፡ ኩባንያው መተግበሪያውን ያበለጸገው ሰዎች ሕይወታቸውን “በስማ በለው” እንዳይመሩ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ዋና መሥሪያ ቤቱ በሳን ፍራንሲስኮ የሚገኘው የታንግል አስተዳዳሪ ዌስት ኮ በድረ ገጹ ላይ እንዳሠፈረው፤ ተልዕኮው “ሰዎች ሕይወታቸውን የበለጠ ዓላማ እንዲኖራቸው የሚረዱ መሣሪያዎችን ማቀበል” እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ስለ መተግበሪያው የተናገረው የትዊተሩ ቢዝ ስቶን፤ የመጀመርያ ሙከራ ደረጃ ላይ ይገኛል ያለው መተገበሪያው፤ በየማለዳው ለተጠቃሚዎች “ዛሬ ምን የማድረግ ዓላማ አለህ/ሽ?” የሚል መልእክት እንደሚልክ ገልጿል፡፡
የቴንግል አስተዳዳሪ የዌስት ኮስት ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመሆን የሚሠሩት የፒንትረስቱ ኢቫን ሻርፕ ናቸው፡፡ በቅርቡ በተላለፈ የፖድካስት ቃለ መጠይቅ ላይ፤ ስልክ እና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን “በመሠረቱ ሰውን በምን ረገድ እንዳስተጓጎሉ ለመረዳት” ለስምንት ዐመታት “ሲብሰለሰሉ” መሰንበታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም “ጥቂትም ቢሆን የተሻለ ለማድረግ ምን መሥራት እንደሚገባን እረዳለሁ” ብለዋል።
አዲሱን መተገበሪያ ያስተዋወቁት ቢዝ ስቶን እና ኢቫን ሻርፕ፤ ቀድሞ በሥራ ላይ ባዋሏቸው መተግበሪያዎች የሰው ልጅ አእምሮ ላይ “ውድመት” ደርሷል በማለት ማርከሻ ነው ያሉትን መሥራታቸው መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ሁለቱም ግለሰቦች በቀድሞ ኩባንያዎቻቸው ወደ ቱጃርነት ተለውጠዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












