Homeዜናና ወቅታዊዜናወደ የመን የሚገቡ ፍልሰተኞች ቁጥር ሲጨምር፤ አብዛኛውን ቁጥር የሚሸፍኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው -...

ወደ የመን የሚገቡ ፍልሰተኞች ቁጥር ሲጨምር፤ አብዛኛውን ቁጥር የሚሸፍኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው – አዲስ ሪፖርት

ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም)፤ የመን የሚገቡ ፍልሰተኞች ቁጥር ማሻቀቡን አዲስ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል። በተጠናቀቀው ታኅሣሥ በየመን የሚገኙ የድንበር ፍሰት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ላይ በታየው የሰዎች እንቅስቃሴ፤ ድንበር አቋርጠው የሚገቡ ፍልሰተኞች ከ21 ሺሕ በላይ መድረሱን አስታውቋል።

ቁጥሩ ካለፈው ኅዳር ወር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት ነው፡፡ የድርጅቱ የድንበር ፍሰት መቆጣጠሪያዎች ላይ የታየው የሰዎች እንቅስቃሴ 21 ሺሕ 996 ሰዎች ወደ የመን ሲገቡ፤ 2 ሺሕ 34 ፍልሰተኞች ደግሞ ከየመን ድንበር አቋርጠው ወጥተዋል። ወደ ሀገሯ ከገቡ ፍልሰተኞች 98 በመቶው  ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል። ቀሪውን ሁለት በመቶ የሚሸፍኑት የሶማሊያ ዜጎች ናቸው። ከየመን አቋርጠው የወጡት ፍልሰተኞችም እንዲሁ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ዜጎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ወደ የመን ከፈለሱት ውስጥ 72 በመቶው መድረሻቸውን ሳዑዲ ዐረቢያ ሲያደርጉ፤ ቀሪዎቹ በየመን ለመቆየት ያለሙ ናቸው። 80 በመቶ መነሻቸው በዋናነት ከጅቡቲ ሲሆን፤ 18 በመቶ ከሶማሊያ ነው። ለፍልሰት ያነሳሳቸው ምክንያት 98 በመቶ የተሻለ የኢኮኖሚ ፍለጋ መሆኑ የአይኦኤም ሪፖርት ይገልጻል። 60 በመቶ ወንዶች ሲሆኑ፤ 23 በመቶ ሕፃናት፣ 17 በመቶ ደግሞ ሴቶች መሆናቸው ተመላክቷል። በኢትዮጵያ ያለውን የሰዎች ዝውውር ሪፖርት ያወጣው ድርጅቱ፤ በጥቅምት ወር ብቻ በአጠቃላይ 45 ሺሕ 150 የሰዎች ዝውውር ተመዝግቧል ብሏል።

በወቅቱ ባወጣው የኢትዮጵያ ሪፖርት ከኢትዮጵያ ከወጡት ፍልሰተኞች መካከል 40 በመቶ መዳረሻ ያደረጓት ሳዑዲ ዐረቢያን መሆኑን ይገልጻል። ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚወጡት ዜጎች በዋነኝነት የሚጠቀሙባቸው የጅቡቲ ድንበር መተላለፊያ የሆኑትን የአፋር ክልሉን ገላፊ እና ደወሌ እንዲሁም የሶማሊያ ድንበር የሆነው ቶጎ ውጫሌ መሆናቸውን አስታውቆ ነበር።

በተያያዘ የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ባለፉት ስድስት ወራት 7 ሺሕ 900 ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ መያዙን ከሁለት ቀን በፊት አስታውቋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular