የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛው ፍርድ ቤት፤ በአብዛኛው ሙስሊም ማንነት ባላቸው የሮሂንጃ ሕዳጣን ዜጎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች በሚል በሚያንማር ላይ የቀረበውን ክስ መስማት የሚጀምረው ዛሬ ሰኞ ነው፡፡ የፍርድ ሂደቱ የዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት (አይሲጄ) የሚመለከተው በዐይነቱ “የመጀመርያው የዘር ማጥፋት” ጉዳይ ነው፡፡ ሊያስከትለው የሚችለው ውጤትም ከምያንማር ባሻገር፤ በጋዛ ላይ በፈጸመችው የዘር ማጥፋት ጦርነት ምክንያት ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል ላይ ያቀረበችውን አቤቱታ ሊነካ የሚችል ነው ተብሏል፡፡ ዛሬ የሚጀምረው ችሎት ለሦስት ሣምንታት ይቆያል።
እ.አ.አ በ2017 በርካታ ቁጥር ያላቸው የሮሂንጃ ሙስሊሞች በምያንማር መንግሥት የተከፈተባቸውን የዘር ማጥፋት በመሸሽ ወደ ጎረቤት ባንግላዴሽ ተሰደዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳለው ከሆነ፤ በሮሂንጃ የምያንማር የፀጥታ ኃይሎች ከሚያደርሱባቸው ስቃይ በመሸሽ ወደ ጎረቤት ሀገር የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከ700 ሺሕ በላይ ነው፡፡
ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሁለት ዐመት በኋላ ጋምቢያ ጉዳዩን ለዓለም ፍርድ ቤት አቅርባለች፡፡ ስደተኞቹ የጅምላ ግድያዎች፣ አስገድዶ መድፈር እና የእሳት ቃጠሎ ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው ተናግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት እውነታ የማፈላለግ ተልዕኮ፤ ጥቃቱ “የዘር ማጥፋት ድርጊቶችን” አካቷል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። ይሁን እንጂ የምያንማር ባለሥልጣናት ድርጊቱን በሮሂንጃ የታጠቁ ቡድኖች ለሰነዘሩት ጥቃት “አጸፋ ለመስጠት” የተደረገ ሕጋዊ “የፀረ ሽብር ዘመቻ ነው” በማለት አስተባብለዋል፡፡ በቅድመ ችሎት ክርክር ወቅትም፤ የወቅቱ የምያንማር መሪ ኦንግ ሳን ሱኪ የጋምቢያን የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ “ያልተሟላ እና አሳሳች ነው” በማለት አጣጥለውታል፡፡

የክሱን መጀመር በተመለከተ ለሬውተርስ የተናገሩት የተባበሩት መንግሥታት ነፃ የምርመራ ኃላፊ ኒኮላስ ኩምጂያን፤ “ጉዳዩ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዴት ብያኔ እንደሚሰጠው፣ እንዴት ሊረጋገጥ እንደሚችል እና ጥሰቶች እንዴት ሊታረሙ እንደሚችሉ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀምጣል” ብለዋል፡፡ በችሎቱ የሮሂንጃ ሰለባዎች ቀርበው ምስክርነት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ጉዳይ ሊኖረው ከሚችለው ተጽእኖ አንጻር ምስክርነት የማሰማት ሂደቱ ለሕዝብ እና ለመገናኛ ብዙኃን ዝግ እንደሚደረግ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ዓለም አቀፉ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ከዚህ ቀደም እንዳሳወቀው፤ ወንጀሎቹ የተፈጸሙት ቲታመድ በተሰኘው በሚያንማር የጦር ኃይል፣ በብሔራዊ የፖሊስ ኃይሎች፣ በድንበር ጥበቃ ፖሊሶች እንዲሁም የሮሂንጃ ማንነት በሌላቸው ሲቪሎች እገዛ ነው፡፡ በግዳጅ እንዲሰደዱ ከተደረጉት ባሻገር ዐሥር ሺሕ ገደማ የሮሂንጃ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳለው ከሆነ፤ የሚያንማር የፀጥታ ኃይሎች በሰሜን ምዕራብ ራኺን ግዛት የቀሩ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ የሚፈጽሙትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አሁንም ድረስ ቀጥለውበታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












