ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሜታ በስሩ ከሚያስተዳድራቸው ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ትሬድ ከግማሽ ሚሊዮን የሚልቁ የአውስትራሊያ ታዳጊዎችን አገልግሎቱን መጠቀም እንዳይችሉ አግዷል። የአውስትራሊያ መንግስት በአለም የመጀመርያ የሆነውን እድሜያቸው ከ16 አመት በታች ለሆኑ ታዳጊ ልጆች የማህበራዊ ሚዲያ የጣለውን ክልከላ ከታህሳስ 1፤ 2018 ጀምሮ ተግባራዊ አድርጓል። የአውስትራሊያ መንግስት እገዳው ያስፈለገው የታዳጊዎችን ደህንነት ለመጠበቅ እንደሆነ አስረድቷል። በዚህም እገዳው ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ በመጀመርያው ሳምንት ወደ 550 ሺህ የሚጠጉ አካውንቶች በሜታ ታግደዋል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ፤ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ዕድሜ የሚያረጋግጠውን አሠራር መዘርጋት ያስፈለገው ታዳጊዎች “ከእውናዊው ዓለም እየተነጠሉ” በመሆኑ ነው ብለው ነበር፡፡ መድረኩ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝ የገለጹት አንቶኒ አልባኒዝ፤ የሚዲያ አማራጩ ሕጻናትን ከእውናዊው ዓለም ከማቆራረጡ በተጨማሪ “ከእውነተኛ ጓደኞቻቸው ጭምር እያራቀ” እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም በማኅበራዊ ሚዲያ ምክንያት ወላጆች ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውንም ተናግረው ነበር።
ይህን ተከትሎም ኩባንያው አዲሱን ህግ በማክበር በመጀመሪያው ሳምንት 330 ሺህ 639 ኢንስታግራም፣ 173 ሺህ 497 ፌስቡክ እና 39 ሺህ 916 Threads ተጠቃሚዎችን ማገዱን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል። በአውስትራሊያ ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 15 ያሉ ከ350 ሺሕ በላይ የኢንስታግራምና ከ150 ሺሕ በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ይፋዊ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሜታ፤ የአውስትራሊያ መንግስት ከኢንዱስትሪው ጋር የደህንነት መስፈርቶችን እንዲጨምሩ፣ ግላዊነትን የሚጠብቁ እንዲሁም እድሜ ተስማሚ ይዘቶችን እንዲያቀርቡ የተሻለ አማራጭ ለማምጣትና ለማበረታታት እንዲሳተፍ ጥሪ እናቀርባለን ብሏል። ሜታን ጨምሮ ኩባንያዎች የታዳጊዎችን ደህንነት ከበይነ መረብ ጥቃት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን የተስማሙ ይሁን እንጂ በመብት ተከራካሪዎችና በአንዳንድ ምሁራን ዘንድ ትችትን እያስተናገደ ይገኛል። በተመሳሳይ ዩትዩብ የአውስትራሊያ መንግስት ያወጣውን ህግ እንደሚያክብር ያስታወቀ ቢሆንም ኩባንያው እገዳው የኢንተርኔት አገልግሎቱን የበለጠ ደህንነቱ የተጠበቀ አያደርገውም ሲል አቋሙን ሲገልጽ ቆይቷል። አንዳንድ ባለሙያዎች የአውስትራሊያ ታዳጊዎች እገዳውን በቀላሉ ማለፍ ይችላሉ የሚል ስጋት አንስተዋል። የእድሜ ማረጋገጥ የሚያካሂደውን ቴክኖሎጂ በማታለል ወይም ሌሎች ደህንነታቸው ያልተጠበቀ ቦታ በመረቡ ላይ ለመሰብሰብ ያጋልጣል ብለዋል።
በወላጆች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ያገኘው ክልከላው ሌሎች አለም ሃገራትም የአውስትራሊያን እርምጃ ለመከተል በቅርበት በመከታተል በማጤን ላይ ይገኛሉ። ከአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት እስከ አውሮፓ ህብረት ድረስ የተለያዩ መንግስታት የልጆችን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ለመገደብ ሙከራ ላይ ናቸው። እንደ ማሌዢያ፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌይ እና ሌሎችም እገዳውን ተግባራዊ ለማድረግ ጫፍ ላይ ደርሰዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












