በደቡብ እስያ ውስጥ በምትገኘው ማልዲቭስ፤ የረመዳን ጾም ማብቂያ ላይ የሚሰብሰበውን “ዘካትል ማል” መሰብሰብ የሚያስችል ዲጂታል ሥርዐት በመላ ሀገሪቱ ለማስጀመር በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ አስታውቃለች፡፡ ሀገሪቱ የምታስጀምረው ሥርዐት፤ “የሃይማኖታዊ ጉዳዮች አስተዳደርን ለማዘመን” የሚደረገው ጥረት አካል ነው ተብሏል፡፡
አሠራሩ የሚጀመረው የማልዲቭስ ዘካ ሰብሳቢው አካል “ዘካ ሃውስ” እና በቴክኖሎጂ ላይ ከሚሠራ የግል ኩባንያ ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ከተፈራረመ በኋላ ነው፡፡ ስምምነቱ በመላው ማልዲቭስ የዲጂታል የዘካ አሰባሰብ ማዕቀፍ የሚዘረጋ ነው፡፡ በዚህም ምእመናን በመጪው ረመዳን የዘካ ክፍያቸውን በኦንላይን አማራጮች እንዲከፍሉ ያስችላቸዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት የዘካ ክፍያዎች የሚፈጸሙት ያለ ተጨማሪ የአገልግሎት ክፍያ ነው፡፡ በዲጂታል ሥርዓት በኩል የተሰበሰበው ሁሉም ገንዘብ በቀጥታ የሚተላለፈው ወደ ዘካ ሃውስ ይሆናል፡፡ ባለሥልጣናቱ እንዳሉት፤ የክፍያ ሥርዓቱ የተዘረጋው ደኅንነቱ በተጠበቀ፣ ከኢስላማዊ ሕግጋት ጋር በሚስማማ እንዲሁም ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች አስፈላጊ ነው የሚባለውን “ግልፅነት፣ ፍጥነት እና አስተማማኝነት”ን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡
ማልዲቭስ እስልምና ይፋዊ ሀገራዊ ሃይማኖት ነው፡፡ በሀገሪቱ ከሚገኙ ዜጎች ውስጥ 99 ነጥብ 1 በመቶ ሙስሊሞች ናቸው፡፡
ከዘካ ጋር በተገናኘ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዘካና አውቃፍ ኮሚሽን፤ በመጪው የረመዳን ወር የዘካ ማሰባሰብ እንደሚጀመር አስታውቋል፡፡ ይህ የተገለጸው ኮሚሽኑ ጥር 4/2018 ሥራ ማስጀመርያ መርሐ ግብር ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡ ከእስልምን ማእዘናት መካከል አንደኛው የሆነውን የዘካ ሥርዐትን፤ ሀገራት ለማኅበራዊ ፍትሕ ለማስፈን እንደሚጠቀሙበት ይነገራል፡፡

በኢትዮጵያም ይህን ሥርዐት ለማኅበራዊ ደኅንነት የሚኖረውን አስተዋጽኦ ለመጨመር ሥርዐት ሊበጅለት እንደሚገባ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ከዚህ ቀደም አሳስቦ ነበር፡፡ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሑሪያ ዓሊ፤ የማኅበራዊ ደኅንነት ጥበቃን ለማጠናከርና ሚናው አሁን ካለው በላቀ ደረጃ እንዲጎለብት ለማስቻል በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ መሥሪያ ቤታቸው ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዘካ ኮሚሽን ጋር መሥራት እንደሚፈልግም በጥቅምት ወር ተናግረዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












