ዋና መሥራያ ቤቱን ስዊዘርላንድ ያደረገው ዓለም አቀፉ የምግብ እና መጠጥ ማቀነባበሪያ ኔስሌ (Nestle)፤ በ“ናን”፣ በ“አልፋሚኖ”፣ “ኤስ-26 ጎልድ” እና “ኤስ-26 አልቲማ” የምርት ሥያሜዎች ለገበያ የቀረቡ የሕፃናት ወተት (baby formula) “የተወሰኑ ምርቶችን” ደንበኞች እንዳይጠቀሙ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ በምርቶቹ ሳቢያ እስካሁን የተመዘገበ ሕመም አለመኖሩን ያሳወቀው ኩባንያው፤ ማስጠቀቂያውን በመላው ዓለም አሰራጭቷል፡፡
ይህን ተከትሎ የተለያዩ የዓለም ሀገሮች ዜጎች የተከለከሉትን ምርቶች ከመጠቀም እንዲታቀቡና የሕመም ምልክት ካሳዩ ወደ ሐኪም ዘንድ እንዲሄዱ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
ከሀገሮቹ መካከል አንደኛዋ ሳዑዲ ዐረቢያ ነች፡፡ የሳዑዲ ዐረቢያ የምግብ እና የመድኃኒት ባለሥልጣን፤ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡት የኔስሌ የሕፃናት ወተቶች፤ በናን፣ በአልፋሚኖ፣ ኤስ -26 ጎልድ እና ኤስ-26 አልቲማ የምርት ሥያሜዎች የተመረቱ መሆናቸውን በመዘርዘር፤ ዜጎች “የባች ቁጥራቸው” የተዘረዘሩ ምርቶችን ከዚህ በኋላ ከመጠቀም እንዲታቀቡ ማስጠንቀቂያ ማውጣቱን ሳዑዲ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ የጥንቃቄ መልእክቱ የተሰጠው ኩባንያው “በፈቃደኝነት አደጋዎችን ከገመገመ በኋላ” በመጣ መረጃ ላይ የተመሠረተ መሆኑንም አክሏል፡፡
በሳዑዲ ዐረቢያ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የተባሉት የምርት ሥያሜዎች፤ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ በሥፋት የሚታወቁ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ባለሥልጣን፤ እስካሁን ድረስ ምርቶቹን በተመለከተ ያወጣው ማስጠንቀቂያ የለም፡፡
ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የተዘረዘሩት ምርቶች በጀርመን ውስጥ የሚዘጋጁት “ቤባ” እና “አልፋሚኖ” በሚል የምርት ሥያሜ ነው፡፡ ማስጠንቀቂያውን ከኩባንያው ማረጋገጡን የዘገበው ቢቢሲ፤ ምርቶቹ በጀርመን ፈረንሳይ፣ ኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ ጣሊያን እና ስዊድን ጨምሮ በበርካታ የአውሮፓ ሀገሮች ተሽጠዋል ብሏል፡፡
“የሕፃናት ደኅንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው ያለው ኔስሌ፤ “በወላጆች፣ በአሳዳጊዎችና በደንበኞች ላይ ለደረሰው ችግር ከልብ ይቅርታ እንጠይቃለን” ሲል አሳውቋል፡፡
በመላው ዓለም የተሸጡት እነዚህ ምርቶች፤ ከተወሰዱ በኋላ የማቅለሽለሽ እና የማስመለስ ስሜት ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ ለዚህ ሰበብ የሚሆነው ሴሬዩላይድ ነው፡፡ ሴሬዩላይድ በባክቴሪያ የሚመነጭና በምግብ የሚተላለፉ በሽታዎችን የሚያስከትል ንጥረ ነገር ሲሆን፤ የምግብ መመረዝ ምልክቶችን ሊያመጣ ይችላል፡፡ ይህ መመረዝ በሕፃናት ላይ በፍጥነት ሊባባስ የሚችል ማስታወክ እና የሆድ እብጠትን ሊያካትት ይችላል፡፡
የእንግሊዝ የምግብ ደረጃዎች ኤጀንሲ እንዳስጠነቀቀው፤ ሴሬዩላይድ የሕፃናት ወተት (ፎርሙላ) በሚዘጋጅበት ጊዜ በማብሰል ወይም የፈላ ውሃ በመጠቀም ሊጠፋ አይችልም። (ሚንበር ቲቪ)












