በዓለም የችርቻሮ ንግድ ቀዳሚ ከሆኑት አንዱ የፈረንሣዩ ኬርፎር ግሩፕ፣ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር ከሚተዳደረው ኩዊንስ ሱፐር ማርኬት ጋር የቢዝነስ ቅንጅት (ፍራንቻይዝ) ስምምነት መፈራረሙን ይፋ አድርጓል። ስምምነቱን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አሕመድ መፈራረማቸውን ሚድሮክ ታኅሣሥ 27/2018 አስታውቋል፡፡
ሚድሮክ፤ “የመጀመርያውን ዓለም አቀፍ ፍራንቻይዝ ለኢትዮጵያ ገበያ የሚያስተዋውቅ ነው” ያለው ስምምነት፤ በኩባንያው “የዕድገት ጉዞ ላይ ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት” መሆኑንም ገልጿል፡፡
በስምምነቱ መሠረት፤ ኩዊንስ ሱፐር ማርኬት የኬርፎርን ሥያሜ እና ዓርማ፣ የኩባንያውን የችርቻሮ ንግድ ዕውቀት እና ዓለም አቀፍ የአሠራር መስፈርቶችን በኢትዮጵያ በሚገኙ የሱፐር ማርኬት ቅርንጫፎቹ ላይ ተግባራዊ ይደረጋል። በአሁኑ ሰዐት በኢትዮጵያ የሚገኙ 13 የኩዊንስ ሱፐር ማርኬት ቅርንጫፎች በሙሉ ወደ ኬርፎር ንግድ ሥያሜ ይቀይራሉ። የመጀመሪያዎቹ መደብሮች ክረምት ሊቃረብ ሲል ሥራ ይጀምራሉ ተብሏል። በሁለት ዐመት ውስጥ ተጨማሪ 17 አዳዲስ መደብሮችን በመክፈት ጠቅላላ የቅርንጫፎቹን ብዛት 30 ለማድረስ በእቅድ አስቀምጧል፡፡
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አሕመድ፤ ስምምነቱ ሚድሮክ የሚያመርታቸውን እንደ ቡና፣ ሻይ፣ ቅመማ ቅመም፣ አበባ እና ፍራፍሬ ያላቸው ምርቶች በኬርፎር ዓለም አቀፍ መረብ አማካኝነት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የኬርፎር ኢንተርናሽናል ፓርትነርሺፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፓትሪክ ላስፋርጉዌስ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ካለው ግንባር ቀደም ከሆነው የችርቻሮ ንግድ ተዋናይ ጋር ይህን ትብብር በመጀመራቸው “ደስተኛ” መሆናቸውን በመግለጽ፤ ሚድሮክ በዘርፉ ያለውን የላቀ እውቀት እና ካርፎር ያለውን ዓለም አቀፍ ልምድ በማቀናጀት ለኢትዮጵያውያን ደንበኞች ጥራት ያላቸው ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡
ኬርፎር ግሩፕ ዋና መሥሪያ ቤቱ የሚገኘው በፈረንሳይ ማሲ ውስጥ ነው፡፡ ኩባንያው የሐይፐር ማርኬቶች፣ የሸቀጣሸቀጥ ሱቆች እና የችርቻሮ ሱቆች ሰንሰለት ላይ ይሠራል። ግሩፑ በ40 ሀገሮች ውስጥ 14 ሺሕ መደብሮች አሉት፡፡ በገቢ በዓለም ላይ ሰባተኛው ትልቁ ቸርቻሪ ኩባንያ ነው። ኩባንያው በአፍሪካ በሰሜን አፍሪካዎቹ ግብጽ፣ ቱኒዝያ፣ ሞሮኮ፣ አልጄሪያ ይገኛል፡፡ በምእራብ አፍሪካ በርካታ ሀገሮች እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ኬንያ እና ዑጋንዳ የችርቻሮ ሱቆች አሉት፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












