የቱርክ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን በተለያዩ ጉዳዮች የአሜሪካው ብሉምበርግ ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት የጽሑፍ ምላሽ፤ በጋዛ ሰላም አስከባሪ ኃይል ጉዳይ የሀገራቸው ሚና የማይተካ መሆኑን ገለጸዋል፡፡ ኤርዶጋን የጠቀሱት የጋዛ ሰላም አስከባሪ፤ በመስከረም ወር በቀረበው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዛ ተኩስ አቁም ላይ የሰፈረ ነው፡፡
የጋዛን ደኅንነት የሚቆጣጠር ነው የተባለው ኃይል፤ አሜሪካ ከዐረብ እና ሌሎች አጋሮቿ ጋር ባንድነት የሚቋቋም ነው፡፡ ይህ ኃይል የረዥም ጊዜ የውስጥ ደኅንነት ለማስፈን መፍትሔ ሰጪ እንደሚሆን ተጠቁሟል። ከግብፅ እና ከእስራኤል ጋር በመሆን የድንበር አካባቢዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ያግዛል የተባለ ሲሆን፤ አዲስ ከሠለጠኑ የፍልስጤም የፖሊስ ኃይሎች ጋር የሚሠራ ነው፡፡
ኤርዶጋን ለብሉምበርግ በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፤ በቀጣናው የሚገኙ ሕጋዊ ያሏቸው ተዋንያን መሳተፍ የሰላም አሰከባሪውን ኃይል ስኬታማነት አልያም አለመሆን ይወስነዋል፡፡ እነዚህ ተዋንያን በግብጽ ሻርም አል ሸይኽ የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት በተፈረመበት ወቅት የተሳተፉ ሀገሮችን የሚያካትት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የሀገራቸውን ተሳተፎ በማጉላት “ቱርክ የሌለችበት ማንኛውም አካሄድ የፍልስጤምን ሕዝብ አመኔታ ለማግኘት አዳጋች ያደርገዋል” ብለዋል፡፡
የፕሬዝዳንቱ አስተያየት የተሰጠው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ቱርክ በሰላም አስከባሪ ኃይሉ ላይ የሚኖራቸውን ተሳተፎ በመቃወማቸው ነው፡፡ ነገር ግን የቱርክ አለመሳተፍ እንደ አዘርባጃን፣ ፓኪስታን፣ ሳዑዲ ዐረቢያ እና ኢንዶኔዥያ ያሉ ሌሎች አጋሮችን ወታደሮችን እንዳይልኩ ያደርጋል፡፡
ባለፈው ወር ኔታንያሁ ከትራምፕ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ የአንካራን ተሳትፎ ላይ ቀይ መስመር ሊያበጁ ሞክረዋል። ይሁን እንጂ ትራምፕ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የቱርክን ተሳትፎ እንደማይከለክሉ ተናግረዋል። የቱርክ ዲፕሎማሲያዊ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ፤ ቱርክ ወታደሮቿን ወደ ጋዛ ለመላክ ሙከራ አላደረገችም፡፡ የፍልስጤሙ ሐማስ በዓለም አቀፍ ኃይል ላይ እምነት የማያሳድር ከሆነ ግን ስምምነቱ ሊፈርስ ይችላል የሚል ሥጋት አላት።
በትራምፕ እቅድ መሠረት፤ ከሰላም አስከባሪ በተጨማሪ ከማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ጋር ግንኙነት የሌለው “ቴክኖክራቲክ” የፍልስጤም አመራር ከጦርነቱ ማብቂያ በኋላ የጋዛን አስተዳደር ይረከባል። ትራምፕ “የሰላም ቦርድ” ሲሉ የጠሩት ይህ አካል፤ ስምምነቱ እንዲሳካ የማድረግና ቁልፍ የቀጣናው እንዲሁም ዓለም አቀፍ መሪዎችን የማሰባሰብ ኃላፊነት እንደሚሰጠው ተናግረዋል። የቁጥጥር አካሉ ሊቀመንበር ራሳቸው እንደሚሆኑም ገለጸዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












