Homeዜናና ወቅታዊዜናአንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከወለድ ነጻ ኢንሹራንስ አገልግሎት ሊጀምር ነው

አንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከወለድ ነጻ ኢንሹራንስ አገልግሎት ሊጀምር ነው

አንበሳ ኢንሹራንሽ ኩባንያ፤ ከወለድ ነፃ ኢንሹራንስ (የተካፉል ኢንሹራንስ) አገልግሎት ለመጀመር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያቀረበው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ ባንኩ ይህን ያስታወቀው በአዲስ አበባ ባካሄደው 18ኛ የባለአክሲዮኖች መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው፡፡

በዚህም መሠረት በቀጣይ ሣምንታት በተካፉል ኢንሹራንስ ዘርፍ ለሚጠቀሙ ደንበኞቹ አገልግሎቱን መስጠት ይጀምራል ተብሏል፡፡

በኢስላማዊ አስተምሕሮ ላይ የተመሠረተው የተካፉል አገልግሎት፤ የመድን ሽፋን የሚሳተፉ ደንበኞች ከወለድ ነጻ በሆነ መንገድ ለሚያዋጡት ገንዘብ፤ ከመድን ሽፋኑ የሚያገኙትን ትርፍና ከካሣ ክፍያ ቀሪ የሆነውን ገንዘብ ደንበኞች ባዋጡት የገንዘብ መጠን ልክ የሚከፋፈሉት የመድን አገልግሎት ዐይነት ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሸሪዓ ሕግን መሠረት ያደረገው ከወለድ ነጻ የመድን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው መመርያ ሲወጣ፤ የ“ተካፉል” የመድን ሽፋን ለመስጠት ቀድሞ ወደ ሥራ የገባው ግሎባል ኢንሹራንስ ነው፡፡ በሀገሪቱ እስካሁን ድረስ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ የኢንሹራንስ አገልግሎት ሰጪ ሥራ ለመጀመር እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ቢገልጽም ወደ ሥራ አልገባም፡፡

በኢትዮጵያ ሥራ ለመጀመር በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ የተነገረው 83 ባለድርሻዎችን ያቀፈው አማና ኢንሹራንስ የተሠኘ ኩባንያ ነው፡፡ ከባለድርሻዎቹ መካከል በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ከሚሰጡ አራት ባንኮች ውስጥ ሦስቱ ይገኙበታል። እነዚህ ባንኮች ሂጅራ፣ ራሚስ እና ሸበሌ ሲሆኑ፤ ያላቸው የድርሻ መጠን አምስት በመቶ ነው።

በመሥራቾቹ መረጃ መሠረት፤ የአማና ኢንሹራንስ የመጀመርያ የተከፈለ የካፒታል መጠን 260 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ነው። ይህ መጠን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያስቀመጠው ዝቅተኛው የ400 ሚሊዮን ብር መስፈርት ላይ ባይደርስም ካፒታሉ የተሰበሰበው ከአዲሱ ደንብ በፊት በመሆኑ ኩባንያው መስፈርቱን ለማሟላት ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ጊዜ እንዳለው ተገልጾ ነበር፡፡ አዲስ መጪው አማና ኢንሹራንስ የሚመራው በዘርፉ ለረዥም ጊዜ ልምድ ባላቸው የቀድሞው የሱዳን ዩናይትድ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሱዳናዊው ዙሃይር ሐሰን ነው።

‘አማና ተካፉል ኢንሹራንስ’ በሚል መጠሪያ የተቋቋመው ኩባንያው፣ በብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሠረት ሥያሜውን ‘አማና ኢንሹራንስ’ በሚል ተክቷል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular