ዛሬ ሐሙስ እ.አ.አ ዲሴምበር 18/2025 ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕለቱን የዐረቢኛ ቋንቋ ቀን በሚል ሠይሞታል። ዐረቢኛ ቋንቋ የተባበሩት መንግሥታት ቀድሞ ይጠቀምባቸው ከነበሩት አምስት የሥራ ቋንቋዎች መካከል ስድስተኛው ሆኖ የተካተተው በ1973 ነው። ከ2012 ጀምሮ ቀኑን ታስቦ እንዲውል ያደርጋል።
ቀኑ በየዓመቱ በተለያየ መሪ ቃል ይከበራል። አምና ከአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ጋር ተቆራኝቶ የነበረው ክብረ በዓል፤ ዘንድሮ መሪ ቃሉ ከፈጠራ (Innovation) ጋር ተገናኝቷል። በዚህ መሪ ቃል ሲታሰብ ዓላማው በትምሕርት፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በቴክኖሎጂ እና በፖሊሲዎች አማካኝነት ዐረቢኛን ይበልጥ ተደራሽ፣ ተለዋዋጭ እና ማኅበራዊ መፍትሔ ሰጪ በሆነ መንገድ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ማሣየት ነው።
ዐረቢኛ ቋንቋ በመላው ዓለም 450 ሚሊዮን ተናጋሪ ያለው መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ቋንቋው ለዕውቀት ልውውጥ፣ ለሥልጣኔ፣ ለሥን እና ኪን ጥበባት፣ ፍልስፍና ወዘተ ጉልሕ ድርሻ አበርክቷል።
ከሴማዊ ቋንቋዎች ውስጥ ከፍተኛ የተናጋሪ ቁጥር ያለው ዐረቢኛ፤ ለዘመናት በኅብረተሰቦች እና በሌሎች ቋንቋዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የቋንቋ ሊቃውንት ይናገራሉ። ሊቃውንት የዐረቢኛ ቃላት በሌሎች ቋንቋዎች ውስጥ የገቡት በንግድ፣ በትምህርት እና በባሕል ልውውጥ አማካኝነት መሆኑን ይገልፃሉ። እንግሊዝኛ፣ ስፓኒሽ፣ ፈረንሣይኛ፣ ቱርክኛ እና ሌሎች በርካታ ቋንቋዎች በሺሕዎች የሚቆጠሩ ቃላትን ከዐረቢኛ ተውሰው በዕለት ተዕለት ግንኙነት መጠቀሚያ አድርገዋል።
ዐረብኛ ለዓለም ካበረከታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦዎች መካከል የሒሳብና ሣይንስ መስክ ያሣረፈው አሻራ ተጠቃሽ ነው። በመስኮቹ የሚታወቁ አንዳንድ ቃላት መሠረታቸው ዐረቢኛ ቢሆንም በጊዜ ብዛት ከእነዚህ ቃላት መካከል አንዳንዶቹ ተቀያይጠውና ተለውጠው አመጣጣቸው ተዘንግቷል።
በምሣሌነት ከሚጠቀሱት ውስጥ በሒሳብ የሚታወቀው “አልጄብራ” ይገኝበታል። ቃሉ የመጣው ከዐረቢኛው “አልጃብር” ሲሆን፣ ትርጉሙ መመለስ ወይም መገናኘት እንደ ማለት ነው። ከሣይንስና ከሒሳብ ባሻገር በዕለት ተዕለት ቃላቶች ውስጥ ተመሣሣይ ሒደት ሊስተዋል ይችላል።
“አልጎሪዝም” (algorithm) የሚለው ቃል የተገኘው ደግሞ በዘጠነኛው መቶ ዘመን በባግዳድ ይኖር በነበረው የፋርስ ምሑር በሙሐመድ ኢብኑ ሙሳ አል ኸዋሪዝሚ ከተጻፈው የእኩልዮሽ መፍትሔ የሚሰጥ ሥራውን አርእስት በመዋስ ነው። “ካራት” (Carat) የሚለው የከበሩ ድንጋዮች ክደት መለኪያም መነሻው “ቂራጥ” قيراط የተባለው የዐረብኛ ቃል ነው።
አንዳንድ ቃላት ደግሞ ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር ሲቀያየጡ ድምጸታቸው ይቀየራል። ለአብነት የእንግሊዝኛው “ጂራፍ” (giraffe) [በአማርኛ ቀጭኔ] የመጣው ከዐረቢኛው “ዘራፋ” زرافة ሲሆን፣ እንግሊዝኛና ሌሎች የአውሮፓ ቋንቋዎች ተመሣሣይ ቃላትን ከራሳቸው ድምጸት ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ የመጀመሪያዎቹን ድምጾች በመቀየር ለውጥ አድርገውበታል።
አንዳንድ ቃላት በንግድ አማካኝነት ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር ተቀያይጠዋል። ለዚህ ተጠቃሹ “ታሪፍ” (Tariff) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ነው። ቃሉ “ታዕሪፍ” تَعْرِيف ከሚለው የዐረብኛ ቃል የተወሰደ ነው። ትርጉሙ “ማሳወቅ” እንደማለት ነው።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዐረቢኛ ቋንቋ ቀን ዋንኛ አስተባባሪ በስሩ የሚገኘው የትምሕርት፣ የሣይንስና የባሕል ድርጅት (UNESCO) ነው። (ሚንበር ቲቪ)












