Homeዜናና ወቅታዊዜናኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያና ሶማሊያ አስከፊ ድርቅ ሊከሰት ይችላል - የተመድ የምግብ እና...

ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያና ሶማሊያ አስከፊ ድርቅ ሊከሰት ይችላል – የተመድ የምግብ እና የእርሻ ድርጅት

በተባበሩት መንግሥታት ስር የሚገኘው የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (FAO)፤ በተያዘው ዓመት ከጥቅምት እስከ ታኅሣሥ በምሥራቃዊ የአፍሪካ ቀንድ ክፍል የሚጠበቀውን ያህል ዝናብ አለመገኘቱን ገልጿል። በዚህም በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የምግብ ዋስትና አቅርቦት ሥጋት በከፍተኛ መጠን ተደቅኗል ብሏል።

በድርጅቱ የምሥራቅ አፍሪካ አደጋ የመቋቋም ተግባራት ቡድን መሪ ሲሪል ፌራንድ በጄኔቫ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ በሶማሊያ፣ በምሥራቅ ኬንያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ በርካታ አካባቢዎች ከአማካይ የዝናብ መጠን ያገኙት 60 በመቶ ብቻ ነው። የችግሩ ተጎጂ አካባቢዎች ከአማካይ መጠን ከ30 በመቶ በታች የዝናብ መጠን አስመዝግበዋል ያሉት ቡድን መሪው፤ የተወሰኑ አካባቢዎች በተቃራኒው ምንም ዐይነት ዝናብ አለማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

በዚህ ሣቢያ አንዳንድ አካባቢዎች በታሪክ ከፍተኛ ተብሎ እንደተመዘገበው እ.አ.አ ወደ 1981 ድርቅ እያመሩ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ኃላፊው በበርካታ ቦታዎች ይህ ሁኔታ ለሁለትና ሦስት ተከታታይ ወቅቶች ቀጥሏል ብለዋል።

የዝናብ እጥረት በሶማሊያ ሰፊ የሰብል ምርት ኪሳራ ማስከተሉ ሲገለጽ፣ በምሥራቅ እና መካከለኛው ኬንያ ደግሞ ዝቅተኛ የሰብል ምርት ይጠበቃል። በተመሳሳይ በእንስሳት ላይ ጉዳት በማስከተሉ የወተት ምርት መቀነስ እና ሞት ይጠበቃል። በሶማሊያ ከ185 ሺሕ በላይ ሰዎች በድርቅ ምክንያት ሲፈናቀሉ፤ ከዚህ ውስጥ ቢያንስ ከ55 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ወደ ኢትዮጵያ ፈልሠዋል ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል። ከዝናብ እጥረት ጋር በተያያዘ ሞቃዲሾ በኅዳር ወር የድርቅ አደጋ አስቸኳይ ጊዜ አውጃለች።

እንደ አናዶሉ ዘገባ ከሆነ፤ በኬንያ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎች በከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት ተጋላጭ ይሆናሉ። በሶማሊያ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ የምግብ ዋስትና እጦት ሊገቡ እንደሚችሉ ሪፖርቶች አመልክተዋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular