ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጠው ሂጅራ ባንክ፤ ለባለአክሲዮኖች የትርፍ ክፍፍል ለማዳረስና በኢትዮጵያ የባንክ ታሪክ የመጀመሪያ ነው ያለውን ዘካ ለማውጣት ዝግጅቱን አጠናቋል ሲሉ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዓብዱሰላም ከማል ተናግረዋል። ሰብሳቢው ይህን ይፋ ያደረጉት ባንኩ ዛሬ ቅዳሜ ታኅሣሥ 11/2018 በሚሊንየም አዳራሽ እያከናወነ በሚገኘው 5ኛ መደበኛ እና 3ኛ አስቸኳይ የባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ነው።
በሪፖርቱ መሠረት፤ በታሪክ ከፍተኛ ያለውን የተጣራ 721 ሚሊዮን ብር አትርፏል። ከዚህ በተጨማሪም በዘንድሮው ዓመት የቅርንጫፍ ማዕከላቱን በ29 በመቶ በማሳደግ አጠቃላይ ቅርንጫፎችን ወደ 150 ማሳደግ ችሏል።
ሐላል ፔይ የተሠኘውን የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥርም በየጊዜው ዕድገት በማሳየት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ደርሷል። የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በአሁን ሰዓት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተገልጿል።
አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታሉን በወራት ውስጥ ወደ 6 ቢሊዮን ብር በማድረስ ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት መስፈርቱን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
የባንኩ አጠቃላይ ሐብት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 19 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ወደ 4.7 ቢሊዮን ብር ለኢንቨስትመንት የሚውል ነው ተብሏል። የተቀማጭ ገንዘብን መጠኑን በተመለከተም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ሲነፃፀር 91 በመቶ ጭማሪ በማሳየት በአሁኑ ወቅት 15 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መድረሱን ሰብሳቢው ይፋ አድርገዋል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ በጀት በመመደብ 29 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 129 አድርሷል፡፡ ይህንን ቁጥር ወደ 150 በማሳደግ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ ከሚሰጡ ባንኮች በቅርጫፍ ብዛት መሪነቱን ማስጠበቁ ተገልጿል።
የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ ባንኩ ባከናወነው ተግባር ወደ 40 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰብ መቻሉንም አክለዋል።
ሂጅራ ባንክ ሥራ የጀመረው በነሐሴ 2013 ነው። (ሚንበር ቲቪ)












