በሳዑዲ ዐረቢያ ሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ በኮንትራት ወደ ሀገሪቱ ለሄዱ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ማሣሠቢያ ሰጥቷል። በኮንትራት ወደ ሳዑዲ ሄደው አሠሪዎቻቸው ጋር ቢገኙም የተሻለ ሥራ ለማግኘት ኮንትራት አፍርሰው የሚጠፉ ዜጎች ድርጊታቸው ለጉዳት ሊዳርጋቸው እንደሚችልም ማስጠቀቂያ ሰጥቷል።
የኤምባሲው ማሣሠቢያ የመጣው የሳዑዲ ዐረቢያ መንግሥት የሥራ ሕግጋትን ተላልፈዋል ባላቸው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ቁጥጥር ማድረግ ከጀመረ በኋላ ነው።
የሳዑዲ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር፤ ባለፈው ወር ከኅዳር 11 እስከ ኅዳር 27 ባሉት ቀናት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ ለመግባት ሲሞክሩ ነበሩ ያለቻቸውን 1 ሺሕ 667 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውቋል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ የኢትዮጵያውያን ዜጎች ቁጥር 57 በመቶ መሆኑን የሚኒስቴሩ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ከኢትዮጵያውያን በመቀጠል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የመናውያን ከ40 በመቶ በላይ ዜጎቿ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ተጠናክሮ በቀጠለውና በሀገር አቀፍ ደረጃ የነዋሪነት፣ የድንበር እና የሠራተኛ ጥሰቶች ላይ አነጣጥሯል በተባለው ዘመቻ የሳዑዲ መንግሥት “ባለፉት ሁለት ሣምንታት የሀገሪቱን ሕግ ተላልፈው የሚኖሩ 19 ሺሕ 500 ነዋሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ስር” ማዋሉን አስታውቋል። ከእነዚህም ውስጥ በተመሳሳይ ከ50 በመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ኤምባሲው ማክሰኞ ታኅሣሥ 14/2018 ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዜጎች ይህን ውሳኔ በማሳለፋቸው ሳቢያ ለተለያዩ ፆታዊ ጥቃቶች፣ ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለገንዘብ ክሕደት፣ ለሥነ ልቡና ጉዳትና ለሌሎች እንግልቶች ሊጋለጡ ስለሚችሉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስገንዝቧል።
ሠራተኞች ሕጉን ጠብቀው እንዲሠሩ ያሳሰበው ኤምባሲው፤ በዚህ መልኩ አስቸጋሪ ሁኔታ የሚገጥማቸው ከሆነ ለኤምባሲው ማመልከት ወይም በአካል በመቅረብ አስፈላጊውን ድጋፍ በማግኘት መብታቸውን ማስከበር እንደሚችሉ ገልጿል።
በሌላ በኩል መንግሥት በሳዑዲ ዐረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገር ውስጥ እየመለሰ እንደሚገኝ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል። በዚህም ሰኞ ኅዳር 13፤ በሀገሪቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ ያላቸውን 2 ሺሕ 595 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመልሠዋል። ከመስከረም የመጀመርያ ቀናት አንስቶ በጀመረው ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ሥራ እስካሁን ድረስ 32 ሺሕ 176 ኢትዮጵያውያን ተመልሠዋል።
ሚክስድ ኢሚግሬሽን ሴንተር እ.አ.አ በ2023 ባወጣው ሪፖርት መሠረት፤ በሳዑዲ ዐረቢያ ከ750 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ። ወደ 60 በመቶ ገደማ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ወደ ሀገሪቱ የገቡ ሊሆኑ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል። (ሚንበር ቲቪ)












