Homeዜናና ወቅታዊዜናድንበር አቋርጠው የሚወጡ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ቁጥር ማሻቀቡን አዲስ ሪፖርት አመለከተ

ድንበር አቋርጠው የሚወጡ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ቁጥር ማሻቀቡን አዲስ ሪፖርት አመለከተ

ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም)፤ በኢትዮጵያ በሚገኙ ስድስት የድንበር ፍሰት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ላይ የታየው የሰዎች እንቅስቃሴ ድንበር አቋርጠው የሚወጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በከፍተኛ መጠን ማሻቀቡን አመልካች መሆኑን ይፋ አድርጓል።

በድርጅቱ የድንበር ላይ ዝውውሮች መቆጣጠሪያ ልኬት ሪፖርት መሠረት፤ በጥቅምት ወር ብቻ በአጠቃላይ 45 ሺሕ150 የሰዎች ዝውውር ተመዝግቧል። ይህም በቀን በአማካይ 1 ሺሕ 156 ሰዎች ድንበር እንደሚያቋርጡ የሚያሣይ ነው። በሪፖርቱ የተገለጸው የሰዎች ዝውውር ከቀደመው መስከረም ወር ጋር ሲነጻጸር በ26 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ከዚህ የሰዎች ዝውውር አኅዝ 78 ሺሕ 3 በመቶው ማለትም 35 ሺሕ 341 ሰዎች ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የወጡ ሲሆን፣ ቀሪው 21 ነጥብ 7 በመቶው ወይም 9 ሺሕ 809 ሰዎች ደግሞ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ናቸው።

ከሀገር ወደ ውጭ የሚወጡት ዜጎች በዋነኝነት የሚጠቀሙባቸው የጅቡቲ ድንበር የሆኑት ገላፊ እና ደወሌ እንዲሁም የሶማሊያ ድንበር የሆነው ቶጎ ውጫሌ ጣቢያዎች ናቸው። እነዚህ መስመሮች 53 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ፍልሰት ተመዝግቦባቸዋል።

በሱዳን ድንበር በሚገኘው በመተማና ኩርሙክ በኩልም 31 በመቶ የሚሆኑት ወጥተዋል ተብሏል። ለዚህም በስደተኞቹ መነሻ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ መባባስና ወቅታዊ ሁኔታዎች እንደ ዋና ምክንያት ተጠቅሷል። ስደተኞቹ ለፍልሰት የሚያነሳሷቸው ዋነኛ ምክንያት 59.8 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መሆናቸውን ሪፖርቱ አክሏል።

ከሀገር የወጡት ስደተኞች መካከል 40 በመቶ መዳረሻ ያደረጓት ሀገር ሳዑዲ ዐረቢያ ነች። 21 በመቶ ወደ ሱዳን ያመሩ ሲሆን፣ በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ የተጓዙት 10 ነጥብ 8 በመቶውን ሸፍነዋል።

በተለይም ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የሚደረገው ጉዞ አብዛኛውን ጊዜ በየመን በኩል የሚያቋርጥ በመሆኑ ከፍተኛ ሥጋት የሚጋርጥ መስመር መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular