በሥሩ 57 ሀገሮችን በአባልነት ያቀፈው የእስላማዊ ትብብር ድርጅት፤ እስራኤል ለራስ ገዟ ሶማሊላንድ እንደ ገለልተኛ ሀገር ዕውቅና መስጠቷን አዲስ ባወጣው መግለጫ “በጥብቅ” አውግዟል። ውሳኔውን “የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት” የሚጥስ ነው በማለት ኮንኖታል።
ድርጅቱ ከሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ጋር “እንደሚተባበር፣ ለሉዓላዊነቱ እና ለግዛት አንድነት እንዲሁም ለሕጋዊ ተቋማት” ያለውን “ድጋፍ” በድጋሚ አረጋግጧል።
ከአባል ሀገሮች ውስጥ 48 ሙስሊም ሀገሮችን ያካተተው ድርጅቱ፤ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ “ደኅንነትን፣ ሰላምን እና መረጋጋትን የመጠበቅ አስፈላጊነት ላይ” አፅንዖት በመስጠት፣ “የቀጣናውን መረጋጋት ሊያዳክሙ የሚችሉ ማናቸውንም ድርጊቶች” ውድቅ አድርጓል።
ሶማሊላንድ የመጀመርያውን የሀገርነት ዕውቅና ማግኘቷ ይፋ የተደረገው ትናንት ጁመዓ ታኅሣሥ 17/2018 ነው። ከእስራኤል ዕውቅና ስታገኝ በምትኩ ለእስራኤል ዕውቅና ሰጥታለች።
ሶማሊላንድ የግዛቴ አካል ነች የምትላት ሶማሊያ፤ ለእስራኤል እስካሁንም ድረስ ዕውቅና ከነፈጉ ሀገሮች መካከል ተጠቃሽ ነች። ሶማሊላንድ እና እስራኤል አንዳቸው ለሌላኛቸው የሀገርነት ዕውቅና የመስጠት ስምምነቱ በኦንላይን የተፈረመው በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና በሶማሌላንዱ ፕሬዝዳንት ዓብዲራሕማን ሙሐመድ ዓብዱላሂ አማካኝነት ነው።
ለሶማሊላንድ የሀገርነት ዕውቅና የሰጠችው እስራኤል፤ ከዓለም ሀገሮች መካከል በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ እና በእስያ አሕጉር ውስጥ ራሷ ዕውቅና ተነፍጋለች። ከሶማሊያ በተጨማሪ ሳዑዲ ዐረቢያ፣ አፍጋኒስታን፣ አልጄሪያ፣ ባንግላዴሽ፣ ብሩኒ፣ ኮሞሮስ፣ ጂቡቲ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ ኩዌት፣ ሊባኖስ፣ ሊቢያ፣ ማሌዥያ፣ ማሊ፣ ሞሪታኒያ፣ ኒጀር፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ኦማን፣ ፓኪስታን፣ ኳታር፣ ሶሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ቬንዙዌላ እና የመን ለእስራኤል ዕውቅና አልሰጡም። (ሚንበር ቲቪ)












