Homeዜናና ወቅታዊዜናኢትዮ ቴሌኮም የአገልግሎት ዋጋ ጭማሪ አደረገ

ኢትዮ ቴሌኮም የአገልግሎት ዋጋ ጭማሪ አደረገ

መንግሥታዊው የቴሌኮም አቅራቢ ኩባንያ ኢትዮ ቴሌኮም፤ በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የዋጋ ጭማሪው “እየታዩ ያሉትን የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎችን” እንዲሁም “በተለያዩ ምክንያቶች እየጨመሩ ያሉ የካፒታልና የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት” እንደተደረገ ዛሬ ሰኞ ታኅሣሥ 20/2018 ባወጣው አጭር መግለጫ ተጠቅሷል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ባደረገው የዋጋ ማስተካከያ፤ ከዚህ ቀደም በ22 ብር ይሸጥ የነበረው ሣምንታዊ የድምጽ ጥቅል 80 ደቂቃ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ታሪፉ ወደ 25 ብር ከፍ ሲደረግ ደቂቃው ወደ 77 ደቂቃ ዝቅ እንዲል አድርጓል። ከዚህ በፊት የጥቅል አገልግሎት በሚገዛበት ሰዓት ለሌሊት የሚሰጠውን ጉርሻ በግማሽ ሲቀነስ፤ የመልዕክት ሥጦታዎች እንዲቀሩ ተደርጓል።

ኩባንያው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ይጠቀሙባቸዋል ያላቸውን የአንድ ብር፣ የሁለት ብር፣ የአምስት ብር እና የአንድ ሰዓት ጥቅሎች ባሉበት እንዲቀጠሉ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ደንበኞች በቴሌብር ጥቅል ሲገዙ የነበረው የ10 በመቶ ቅናሽ ወደ 20 በምቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል ያለው ኢትዮ ቲሌኮም፤ በርካታ ደንበኞች ይጠቀሙባቸዋል ባላቸው 38 የተለያዩ ጥቅሎች ላይ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ አለመደረጉንም ጠቁሟል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም የዋጋ ጭማሪ የተደረገው በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ውስጥ ሁለተኛው ግዙፍ ኦፕሬተር ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፤ በዳታ ጥቅል አገልግሎቶቹ ላይ ከፍተኛ የተባለ የዋጋ ጭማሪ ካደረገ ከቀናት በኋላ ነው፡፡ ሳፋሪኮም ያካሄደው የዋጋ ለውጥ በዋናነት በአብዛኞቹ ጥቅሎች ላይ ከ20 በመቶ እስከ 82 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ ያስከተለ ነው።

የሳፋሪኮም የዋጋ ጭማሪ የመጣው ኩባንያው መሠረቱን ያደረገባት የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ታኅሣሥ 14/2018 ለአንድ ቀን የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ተገኝተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ሩቶ በወቅቱ በኤክስ ገጽ ባሠፈሩት ጽሑፍ፤ ለኢትዮ ቴሌኮም እና ሳፋሪኮም የኬንያና የኢትዮጵያ መንግሥታት ሙሉ ድጋፍ በማድረግ በቀጥናዊ ገበያዎች ላይ ስትራቴጂካዊ የጋራ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በሚፈልጉበት ጊዜ ለመደገፍ ተስማምተናል ብለዋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular