የትምህርት ሚኒስቴር ለትምህርት ቤቶች መምሕራንና የትምሕርት ቤት አመራሮች፤ ወደ ሞያው ለመግባትም ሆነ ለመቀጠል የሚያስችላቸውን የሞያ ፍቃድ መያዝ የሚያስገድድ ረቂቅ መመርያ በማዘጋጀት ለአስተያየት ክፍት አድርጓል፡፡ ሚኒስቴሩ ረቂቁን ያሠራጨው ታኅሣሥ 20/2018 ነው፡፡
ለትምሕርት ባለድርሻ አካላት በሙሉ አስተያየት እንዲሰጡበት የተበተነው ረቂቅ መመርያ የተዘጋጀው፤ የመምሕራንና የትምሕርት ቤት አመራሮች “የሞያ ፍቃድ አሰጣጥና የብቃት ምዘና ወጥ በሆነ መንገድ ለመተግበር” እንዲሁም “ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት” እንደሆነ ተገልጿል።
“አጠቃላይ ትምሕርት የመምሕራንና የትምሕርት ቤት አመራሮች የሞያ ፍቃድ አሰጣጥ እና እድሳት አፈጻጸም” በሚል የተዘጋጀው ረቂቅ፤ የሞያ ፍቃድ ደረጃዎችን በሦስት የሚከፍል ነው፡፡ በዚህም “የመጀመርያ ደረጃ ፍቃድ”፣ “ሙሉ የሞያ ፍቃድ” እና “ቋሚ የሞያ ፍቃድ” በሚል ዘርዝሯል፡፡ ቀዳሚው ከመምሕራን ትምሕርት ማሠልጠኛ ተቋማት በመምሕርነት አልያም በትምሕርት ቤት አመራርነት ሥልጠና ወስደው ወደ ሞያው ለሚገቡ የትምሕርት ባለሙያዎች የሚሰጥ ነው። የሞያ ፍቃዱ ለሁለት ዓመት ብቻ የሚያገለግል ነው፡፡ ይህ “የመጀመርያ የሞያ ፍቃድ” በመባል የብቃት ምዘናውን ለሚያልፉ ባለሞያዎች ይሰጣል።
ሁለተኛው የሞያ ፍቃድ “ሙሉ የሞያ ፍቃድ” በመባል የሚጠራ ሲሆን፤ ለአምስት ዓመት የሚያገለግል ሆኖ በመጀመርያ የሞያ ፍቃድ ላገለገሉ ባለሞያዎች እንደሚሰጥ በረቂቅ መመሪያው ሠፍሯል፡፡ ሦስተኛ የሞያ ፍቃድ በየአምስት ዓመቱ የሚታደሰው “ቋሚ የሞያ ፍቃድ” በሚል ሥያሜ የተቀመጠ ነው፡፡ ይህ ፍቃድ የሚመዘነው በማሕደረ ተግባር የብቃት ምዘና ነው፡፡ በዚህ ምዘና ተመዛኙ ቢያንስ 70 በመቶ ማስመዝገብ ይኖርበታል፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪም ሞያዊ ሥልጠና ሳይወስዱ በሁኔታዎች አስገዳጅነት በማስተማር ወይም በትምህርት ቤት ውስጥ አመራርነት እንዲያገለግሉ ለሚመደቡ ባለሞያዎች “ጊዜያዊ የሥራ ፍቃድ” እንደሚሰጥ ይጠቅሳል፡፡ ፍቃዱ የማይታደስና ለሁለት አመት ብቻ የሚያገለግል እንደሆነ በረቂቁ ተቀምጧል። እንዲሁም የመጀመርያ እና ሙሉ የሞያ ፈቃድ ደረጃዎች እንደማይታደሱ ተገልጿል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ምዝገባ የሚከናወነው የብቃት ምዘናው፤ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚሰጥ በረቂቁ ተብራርቷል። በረቂቅ መመርያው መሠረት ፍቃዱ በሐሰተኛ ማሰረጃ ከተገኘ፣ ያለአግባብ የተጠቀመ እንዲሁም ሞያውን ለቆ ሲሄድ እንደሚሰረዝ ተገልጿል፡፡
የብቃት ምዘናውን አተገባበር በተመለከተም በተዘጋጀው የመምረጫ መሥፈርት መሠረት ከትምሕርት ቤቶች፣ ከመምሕራን ትምሕርት ኮሌጆች፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከትምሕርት ሚኒስቴርና ከክልል ትምሕርት ቢሮ ከተውጣጡ ባለሞያዎች መካከል የብቃት የጽሑፍ ምዘና ይዘጋጃል ተብሏል፡፡ የመመርያውን አተገባበር የሚቆጣጠር ተጠሪነቱ ለትምህርት ሚኒስቴር የሆነ ካውንስል ይቋቋማል። (ሚንበር ቲቪ)












