የዩናይትድ ስቴትስ ትልቁ ከተማ ከንቲባ ዞሕራን ማምዳኒ፤ ቅዱስ ቁርኣን ተጠቅመው ቃለ መሐላ የፈጸሙ የመጀመርያው የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ መሆናቸው ሲረጋግጥ፤ ቃለ መሐላውን ያስፈጸሙት የኒውዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሌቲሺያ ጄምስ ናቸው፡፡
የ34 ዓመት እድሜ ያላቸው ዞሕራን፤ በአሁኑ ወቅት በከተማው ከንቲባነት መንበር ላይ የተቀመጡ የመጀመርያው ሙስሊም፣ የመጀመርያው የደቡብ እስያ የዘር ግንድ ያለው እንዲሁም የመጀመርያው በአፍሪካዊ የተወለዱ ግለሰብ መሆን ችለዋል፡፡ በመሓላ ሥነ ሥርዐቱ ወቅት የተጠቀሙት ከኒውዮርክ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት በውሰት የተወሰደ የ200 ዓመት እድሜ ጠገብ የቅዱስ ቁርኣን ቅጂ ነው፡፡

ታሪካዊው የቅዱስ ቁርኣን ቅጂ በአንድ ወቅት የጥቁር ታሪክ ተመራማሪ እና ጸሐፊ አርቱሮ ሾምበርግ ንብረት የነበረ ነው፡፡ ተመራማሪው እ.አ.አ በ1926 አራት ሺሕ የመጻሕፍት ስብስብ ለኒውዮርክ ቤተመጻሕፍት ሸጧል፡፡ የሾምበርግ የጥቁሮች ባሕል ምርምር ማዕከል የሚል ሥያሜ የተሰጠው ይህ ስብስብ ነው፡፡ በ1870ዎቹ በፖርቶሪኮ ውስጥ የተወለደው ሾምበርግ፤ ወላጆቹ የጀርመን እና የአፍሮ-ካሪቢያን ዝርያ ያላቸው ናቸው፡፡
ቤተ መጻሐፍቱ ማምዳኒ ከከተማዋ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለውን የሾምበርግን የቅዱስ ቁርኣን ለመሐላ ለመጠቀም ያሳለፈውን ውሳኔ አወድሶታል፡፡ አስተዳዳሪዎቹ በቡናማ ማሸጊያ የተዋበው አነስተኛ መጠን ያለው ቁርኣን፤ ለዕለት ተዕለት ጥናት የተዘጋጀ መሆኑን ገለጸዋል፡፡ ቅጂው በላዩ ላይ ያረፈበት ፊርማ አልያም የተጻፈበት ቀን የለውም፡፡ ነገር ግን የተሠራበት መንገድ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በ“ሱሪያ ዑስማንያ” (ኦቶማን ሶሪያ) እንደተዘጋጀ ጠቋሚ መረጃዎች አሉት ብሏል፡፡
የቤተመጻሕፍቱ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አንቶኒ ዋ ማርክስ፤ ማምዳኒ የመረጡት የሾምበርግ የቅዱስ ቁርኣን ቅጂ “አካታችነትን፣ ውክልና እና ሲቪክ አስተሳሰብን ወካይ ነው” ብለውታል፡፡

አዲሱ ከንቲባ ነገ ጁመዐ በኒውዮርክ ከተማ አዳራሽ በሚከበረው በዐለ ሲመት ሥነ ሥርዓት ላይ የወንድ እና ሴት አያታቸውን ሁለት የቅዱስ ቁርኣን ቅጂዎች ለመጠቀም በእቅድ እንደያዙ የአልጀዚራ ዘገባ ያመልክታል፡፡
እስራኤል በፍልስጤማውያን የምትከተለውን ፖሊሲና በጋዛ ላይ የምትፈጽመውን የዘር ማጥፋት ጦርነት አጥብቆ በመተቸት የሚታወቁት ዞሕራን ማምዳኒ፤ በምርጫ ዘመቻ ወቅት እስልምናውን በማጉላት፤ ”የሆንኩትን፣ የምመገብበትን መንገድ ወይም የራሴ ነው ብዬ የምኮራበትን እምነት አልለውጥም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
አሁን ባለው ሕግ መሠረት የኒውዮርክ ከንቲባ ለሁለት ተከታታይ የአራት ዓመት የሥልጣን ዘመን መመረጥ ይችላል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












