ሩሲያ የእስላማዊ ባንክ አገልግሎት ልታስጀምር መሆኑን የተናገሩት፤ የሩሲያ ባንኮች ማኅበር ምክር ቤት ሊቀመንበርና የፋይናንስ ገበያ ኮሚቴ ኃላፊ አናቶሊ አክሳኮቭ ናቸው፡፡ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት፤ አገልግሎቱን በሥራ ላይ እንዲውል ጥረት ማድረግ የጀመሩት በሩስያ የሙስሊሞች ቁጥር እያሻቀበ በመምጣቱ መሆኑ ተገልጿል፡፡
አክሳኮቭ በካዛን እስላማዊ የፋይናንስ ተቋማት የሒሳብ እና ኦዲት ድርጅት ማዕከል ባደረጉት ንግግር፤ በሩሲያ እስላማዊ ባንክ ለማቋቋም በሀገሪቱ ከሚገኙ የንግድ መሪዎች እና የሙስሊም ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ምክክር እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ አክለውም “በሩሲያ ውስጥ እንደዚህ ዐይነት ባንክ ለማቋቋም ከዐረብ ሀገሮች ጋር ድርድር እያደረግን ነው፤ በእቅዳችን መሠረት በአንደኛው የዐረብ ሀገር ውስጥ ቅርንጫፍ ባንክ ሊኖረን ይችላል” ሲሉ ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡
የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ በቀዳሚ ድርድር ላይ ይደግፈናል ያሉት ኃላፊው፤ በዚህም መሠረት በሩሲያ የሽርክና ፋይናንስ ልማት ላይ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ተቋም ይቁቋማል ብለዋል። የአጋርነቱ የገንዘብ ገበያ መጠን 12 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚገመት ገልጸዋል፡፡
በሩስያ፤ በሕግ የተደገፈና ለመጀመሪያ ጊዜ አዋጭነትን ለመገምገም ያለመ የእስላማዊ ባንኮችን የሚያስተዋውቅ ፕሮግራም በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የተፈረመ ሕግ ወጥቶ ነበር። ይህን ተከትሎም ሀገሪቱ እስላማዊ የባንክ አገልግሎትን ለመጀመርያ ጊዜ በነሐሴ 26/2015 ይፋ አድርጋለች። የባንክ አገልግሎት ሙከራው ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ነው።
በወቅቱ የሙከራ ፕሮግራሙ ውስጥ የተካተቱት አራት ሙስሊሞች አብላጫ ቁጥር የሚይዙባቸው የሩሲያ ግዛቶች ማለትም ታታርስታን፣ ባሽኮርቶስታን፣ ቼችኒያ እና ዳግስታን ናቸው፡፡ ግዛቶቹ ቀደም ሲል በእስላማዊ የፋይናንስ ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ አላቸው። በፕሬዝዳንቱ ተፈርሞ የተጀመረው ፕሮግራም ስኬታማ ከሆነ በቀሪው የሀገሪቱ ክፍል በቀጣይነት ይጀመራል ተብሎ ነበር፡፡
በ2025 ይፋ በተደረገ ሪፖርት መሠረት፤ የሩሲያ ሙስሊም ሕዝብ ቁጥር ወደ 20 ሚሊዮን ገደማ ይገመታል፡፡ ይህም ከጠቅላላው የሕዝብ ብዛት ከ14 እስከ 15 በመቶ የሚሸፍን ነው፡፡ በሙስሊም ማኅበረሰብ ውስጥ ያለው ከፍተኛ የልደት ምጣኔና በፍልሰት የሚገቡ ሰዎች ቁጥር መጨመር አሐዙን ሊያሳድገው እንደሚችል ትንበያዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ እስልምናን በሩሲያ ውስጥ ሁለተኛው ትልቁ ሃይማኖት ያደረገው ሲሆን፤ የወደፊት የሕዝብ ብዛት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል ተብሎ ይጠበቃል። ለሥራ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ የሕንድ እና ፓኪስታን ዜጎችም ቁጥሩን ይበልጥ ሊያሳድጉት እንደሚችሉ ራሽያስ ፒቮት ቱ ኤዥያ የተሰኘ ድረ ገጽ ዘገባ ያመለክታል፡፡
የሰሜን ካውካሰስ፣ ቼቼኒያ፣ ዳጌስታን፣ ኢንጉሺያ፣ ቮልጋ ክልል፣ ታትራስታን እና ባሽኮርቶስታ፣ በርካታ የሩሲያ ክልሎችን ጨምሮ በበርካታ የሩስያ አካባቢዎች ሙስሊሞች በብዛት ይኖራሉ። (ሚንበር ቲቪ)












