የፍልስጤሙ ሐማስ የእስራኤል ጦር ጋዛን ሙሉ ለሙሉ የሚለቅ ከሆነ ለዐሥር ዓመት የሚዘልቅ የተኩስ አቁም ዕቅድ (ሁድናህ) ምክረ ሐሳብ ለአደራዳሪዎች አቅርቧል። ቡድኑ መሣሪያዎቹን ወደ ምሽግ የመመለስ ፍላጎቱንም አስታውቋል።
ሚድል ኢስት ዐይ በሒደቱ ላይ የተሣተፉ ሥማቸው ያልተጠቀሰ ከፍተኛ የፍልስጤም ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የቡድኑ ዕቅድ ባለፈው ሣምንት በካይሮ ለግብጽ፣ ኳታር እና ቱርክ አደራዳሪዎች ቀርቦ ተደምጧል። ቡድኑ ያቀረበው ሁድናህ በእስልምና ታሪክ ውስጥ በጦርነት ወቅት ሲተገበር የቆየ ነው። በታሪክ ከተመዘገቡት መካከል ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በሁደይቢያህ ዘመቻ ወቅት ከቁረይሽ ጎሳዎች ጋር የተፈራረሙት ተጠቃሽ ነው። ድርሣናት እንደሚያስረዱት ስምምነቱ ‘ሱልህ’ በመባል እንደሚጠራው ዘላቂ የሰላም ስምምነት አይደለም። ስልቱ አቅምን እንደገና በማደራጀት በተሻለ ሁኔታ ለመደራደር እንደ ረፍት የመውሰጃ አጋጣሚ ተደርጎ ይታሠባል።
እንደ ፍልስጤሙ ባለሥልጣን ገለፃ ሁድናህ ከተፈረመ የሐማስ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ ቃታ ከመሣብ ከመታቀብ ባለፈ የጦር መሣሪያዎቹ ተደብቀው ይቆያሉ። ቡድኑ የፈረመውን ቃል ኪዳን ተግባራዊ ማድረጉን አደራዳሪዎች በቀጥታ ቁጥጥር ያደርጋሉ። በዚህ ረፍት ከሁለት ዓመት በላይ በጦርነት ውስጥ ያለፈችው ጋዛና ሕዝቧ ከከበባና መፈናቀል ፋታ በመውሰድ ወደመልሶ ግንባታና መደበኛ አስተዳደር ትመለሣለች።
በቅርቡ በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀረበው የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት ትጥቅ ይፈታል ተብሎ የነበረው ሐማስ፤ እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ ሉዓላዊ በሆነው የፍልስጤም መንግሥት በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጠ አመራር ሥልጣን ካልሆነ በስተቀር የጦር መሣሪያዎቹን ለማስረከብ ፍቃደኛ አልሆነም። እንቅስቃሴው በእስራኤል ላይ የሚያካሂደው የትጥቅ ዘመቻ የሚጠናቀቀው የፍልስጤም መሬት ከወረራ ነጻ ሲሆን ብቻ መሆኑን በተደጋጋሚ በመሪዎቹ በኩል ይገልጻል።
ለሚድል ኢስት ዐይ የተናገሩት የፍልስጤም ከፍተኛ ባለሥልጣን፤ የቡድኑ ባለሥልጣናት የትራምፕ ስምምነት ሰነድ ላይ በተቀመጡት ሐሳቦች ሙሉ በሙሉ ባይስማሙም የፈረሙት ጦርነቱን የማስቆም ዋንኛ ግብ በማስቀመጥ ነው።
በትራምፕ የጋዛ ዕቅድ የእስራኤል ጦር ከተማው እንዲለቅ ቢሠፍርም አሁንም ድረስ ጦሩ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ 53 በመቶውን የጋዛ መሬት በቁጥጥር ስር ማዋሉም በዘገባው ተጠቅሷል። በተጨማሪም በአካባቢው የሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሠማራ ዕቅድ ቢቀርብም የተኩስ አቁም ስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮች እስካሁን ድረስ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ባለመደረጋቸው ወታደሮችን ለመላክ በግልጽ ፍቃደኛ የሆነ ሀገር አልተገኘም። የፍልስጤሙ ባለሥልጣን ስለ ጉዳዩ ሲናገሩ አደራዳሪዎቹ የሰላም አስከባሪውን ኃይል ሐሳብ በወረቀት ቢያቀርቡትም መሬት ላይ የሚታይ ነገር የለም ብለዋል።
ባለሥልጣኑ አያይዘው የገለጹት ሌላው ጉዳይ በአሁኑ ሰዓት በተለይ በአደራዳሪዎች በኩል የተኩስ አቁም ስምምነቱ የተጣሰው በእስራኤል ወገን መሆኑ ላይ መግባባት ላይ መደረሱን ነው። ሐማስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ ግፊት ያሳድራሉ የሚል ዕምነት ቢኖረውም እስካሁን የተሰማ ነገር የለም። በሐማስ አዲስ የተኩስ አቁም ዕቅድ ላይ በእስራኤልና አሜሪካ በኩል የተሰጠ ምላሽ ስለመኖሩ ምንም አልተጠቀሰም። (ሚንበር ቲቪ)












