የኩዌት መንግሥት በእስልምና መምሕርነት ጉልሕ ተፅፅኖ ያሳረፉትን ዕውቁን ዓለም አቀፍ ዳዒ የጧሪቅ ሱወይዳንን ዜግነት መንጠቁን ኩዌት አል የውም የተሠኘው የሀገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ፣ የተነጠቀው የአስ ሱዌይዳን የኩዌት ዜግነት ብቻ ሳይሆን በእርሳቸው አማካይነት ዜግነት ያገኙ ሁሉም ሰዎች ነው። ውሳኔው የተላለፈው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ምክረ ሐሳብ ቀርቦ በካቢኔ ከፀደቀ በኋላ መሆኑ ተገልጿል።
ገልፍ ኒውስ በበኩሉ በአሚር ሸይኽ ሚሻል አል አሕመድ አል ጀበር አል ሰባህ የተፈረመውን አዋጅ ተመልክቻለሁ ሲል አረጋግጧል። የኩዌት ባለሥልጣናት ቀደም ሲል በማጭበርበር፣ የወንጀል ድርጊት ወይም ስጋት በሚጋርጡ ጉዳዮች የተሣተፉ ግለሰቦች ዜግነት ሊሰረዝ እንደሚችል ቢገልፁም፣ በጧሪቅ ሱወይዳን ጉዳይ የሕግ ማብራሪያ አልሰጡም። የዜግነት ንጥቂያው ድንጋጌ በይፋ በጋዜጣ ላይ ከታተመ በኋላ ወዲያውኑ ተግባራዊ ይሆናል።
ሱዌይዳን በሙስሊሙ እና ዐረብ ዓለም ውስጥ ከሚታወቁ ተናጋሪዎች ከፊት ረድፍ ይሠለፋሉ። በመገናኛ ብዙኃን፣ በዳዕዋ እና በሃይማኖታዊ ዲስኩሮች ተፅእኗቸው የጎላ ነው። በአል ሪሳላህ ቴሌቪዥን የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚነትና አቅራቢነት የሠሩት ጧሪቅ፤ በአመራር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተመልካቾችን መድረስ ችለዋል።
እ.አ.አ በ2023 እና በ2024 ከ500 ሙስሊም ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተካተዋል። የሃይማኖት፣ የታሪክና የአመራር መጻሕፍትን ያዘጋጁ ሲሆን፣ በርካታ መጽሐፎች ወደ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ተተርጉመዋል።
በ1953 በኩዌት የተወለዱት አል ሱዌይዳን፣ በ17 ዓመት ዕድሜ ወደ አሜሪካ ከመጓዛቸው በፊት እስልምናንና ሣይንስን በማጣመር አጥንተዋል። ለሁለት አስርት ዓመታት በዚያው አሳልፈዋል። በቱልሳ ዩኒቨርሲቲ በፔትሮሊየም ምህንድስና የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል። (ሚንበር ቲቪ)












