Homeዜናና ወቅታዊዜናከመጪው ሰኞ ጀምሮ የማርበርግ ቫይረስን ምላሽ ለማሳደግ የሚረዳ የሙከራ ክትባት ለተጋላጭ የማኅበረሰብ...

ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የማርበርግ ቫይረስን ምላሽ ለማሳደግ የሚረዳ የሙከራ ክትባት ለተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች ይሰጣል – ጤና ሚኒስቴር

ጤና ሚኒስቴር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ከተማ ተከስቶ ለዜጎች ኅልፈት ሰበብ የሆነውን የማርበርግ ቫይረስ ምላሽ ለማሳደግ የሚረዳ የሙከራ ክትባት፤ ለተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሊሰጥ መሆኑን አስታውቋል። ክትባቱ በአርማወር ሐንሰን የምርምር ተቋም በሚመራ ፈጣን የደረጃ ሁለት ክሊኒካዊ ሙከራ ተደርጎለት ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል፡፡ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደተናገሩት፤ የማርበርግ ቫይረስ ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል የተባለ 2 ሺሕ 500 የማርበርግ ቫይረስ የሙከራ ክትባት ከአሜሪካ መንግሥት በድጋፍ ተገኝቷል፡፡

የአሜሪካ በኢትዮጵያ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ክትባቱን ለኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ተቋም አስረክበዋል። ዶክተር መቅደስ ክትባቱ ከመጪው ሰኞ ኅዳር 29/2018 ጀምሮ መሰጠት ይጀምራል ብለዋል፡፡ ክትባቱ በቅድሚያ የሚሰጠው ለጤና ባለሞያዎችና ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ቡድኖች ነው፡፡ ሚኒስትሯ የምርመራ ተቋሙ ከኢትዮጵያ የምግብ እና የመድኃኒት ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

አምባሳደር ማሲንጋ በበኩላቸው፤ አሜሪካ በባርዳ እና በሳቢን የክትባት ተቋም በኩል ክትባቱን ተደራሽ ማድረጉን በመግለጽ፤ የማርበርግ ወረርሽኝ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ ጠንካራ አጋር መሆኗን ማረጋገጧን ተናግረዋል። ጤና ሚኒስቴር ወርሽኙን ለመግታት ከሚመለከታችዉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ምላሽ በመስጠት ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን መናገራቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡

የማርበርግ ቫይረስ በምርመራ ከታወቀበት ጊዜ ከኅዳር የመጀመሪያ ቀናት አንስቶ እስካሁን 1 ሺሕ 131 የላብራቶሪ ምርመራ ተካሄዷል፡፡ በዚህም 13 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። በቫይረሱ ከተያዙት ስምንቱ ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ አራት ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውን እንዲሁም በሕክምና ሒደት ላይ ያለው አንድ ሰው ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular